የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስምንት የተለያዩ የጤና “ኢንፎርማቲክስ” ሞጅዩሎችን አዘጋጅቶ አስመረቀ
የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ “ሄልዝ ኢንፎርማቲክስ ዲፓርትመንት” ደረጃቸውን የጠበቁ ስምንት (8) የተለያዩ የቅድመ-ምረቃ መማሪያ ሞጅዩሎችን አዘጋጅቶ ጥቅምት18/2013 ዓ.ም አስመርቋል፡፡
በሞጅዩል ምረቃ ስነ-ስርዓቱ የዩኒቨርሲቲውን አካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ አመራሮችና ምሁራን ተገኝተዋል፡፡ “ዩኒቨርሲቲያችን በአለምአቀፍ ደረጃ ምርጥ ከተባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለመካተት ከቻለባቸው መስፈርቶች አንዱ ጥራት ያለው መማር ማስተማር ነው፣” ያሉት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ደግሞ ጥራት ያለው ሞጅዩል መኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
ሞጅዩሎቹ የጤና ኢንፎርማቲክስን ትምህርት ደረጃውን በጠበቀ እና ወጥ በሆነ መልኩ ለመስጠት አላማ አድርገው መዘጋጀታቸውን የህ/ጤ/ሳ/ ኮሌጁና አጠ/ስፔ/ሆስፒታሉ ምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የሞጅዩል ዝግጅቱ ዋና አስተባባሪ ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ አብራርተዋል፡፡ ከተዘጋጁት ውስጥ 4000(አራት ሺ) ሞጅዩሎች ለአስራ አምስት የሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች መሰራጨታቸውንም ዶ/ር ቢኒያም አክለው ገልጸዋል፡፡ የጤና መረጃን በቴክኖሎጂ ማዘመን ላይ ትኩረት አድርገው የተዘጋጁት ሞጅዩሎች ስምንት አይነት ሲሆኑ “Health Operations,Health Program, Routine Health Information System I &II, e-Health, Introduction to Health Informatics, Health Data Analytics and Data Quality and Information Use” የሚሉ ናቸው፡፡
አጠቃላይ የሞጅዩል ዝግጅት ስራው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከዩኒቨርሲቲያችን ጋር በአጋርነት በሚሰራው “DUP” ፕሮጀክት፣ በጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ትብብር የተሰራ ሲሆን፣ የገንዘብ ድጋፍን ያደረገው “ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን”የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡ ስለሆነም በኮሚቴ፣ በድርጅትና በግል ሞጅዩሎቹን በማዘጋጀትና በማስተባበር ሂደት ከፍተኛ ሚና ለነበራቸው አካላት የእውቅና ሰርቲፊኬት ተሰጥቷል፡፡ ********************************************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና አለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ጥቅምት18/2013 ዓ.ም







