የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምና ቡድን የምስጋናና የበዓል ስጦታ ተበረከተለት
በአንጋፋው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተመርቁ በርካታ የህክምና ባለሙያዎች በመስኩ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ተሰማርተው ኮሌጁን ብሎም ሀገራቸውን በጥሩ ስም እያስጠሩ እንደሚገኙ እናውቃለን፡፡

የዩኒቨርሲቲው የህክምና ባለሙያዎች ለሙያው ስነ- ምግባር በመታመንና በመገዛት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ዘመቻ ግንባር ቀደም ድርሻቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ባለሙያዎቹ ከህብረተሰቡ ተነጥለው በቫይረሱ የሚያዙ ህሙማንን ለማከም ሙሉ ጊዜአቸውን መስዋዕት በማድረግ ላይ ናቸው። በዚህ በጎና ጠንካራ ተግባራቸው አሁንም ተቋማቸውን በጥሩ ሁኔታ እያስጠሩ ይገኛሉ፡፡

ስለሆነም ተናበው በመስራት ላይ የሚገኙት የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከሌሎች የመንግስት ኃላፊዎች ጋር በመተባበር የአዲስ ዓመት በዓልን አስመልክቶ የህክምና ቡድኑን ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝታቸውም ሁሉም የቡድኑ አባላት ሙያዊና ሀጋረዊ ኃላፊነታቸውን በከፍተኛ ኃላፊነት በመወጣት ላይ በመሆናቸው ልባዊ ምስጋና አቅርበውላቸዋል፡፡ በማንኛውም መልኩ ሁሌም ከጎናቸው እንደማይለዩ ቃል ገብተዋል፡፡

ከፍተኛ አመራሩ ከባለ ሀብቶች የተለገሰዉን የበዓል ስጦታም (የሰንጋና የታሸጉ የውሀ መጠጦች) አበርክቷል፡፡ የፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤት አቶ እባቡ ሀሽም፣ የጃንተከል ሆቴል ባለቤት አቶ ተመስገን ሰጥአርገውና አቶ ቻሌ አገኘሁ (በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ግለሰብ) ህክምና ባለሙያዎችን በማስታወስ ስጦታውን በመለገሳቸው በአመራሩ በኩል ከፍተኛ ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡
እራሳቸውን ከህብረተሰቡ ነጥለው ቫይረሱን ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲው የህክምና ቡድን አባላት፣ ስለ ተደረገላቸው ሁሉ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፣

“ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ አብሮ በመቆም ይኸን አስከፊ ወቅት መሻገር ይገባል::” የዘወትር መልዕክታችን ነው፡፡



