
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅና አጠ/ስ/ሆስፒታል “Clinical Trial Center” የምርምር ማዕከል አስጀመረ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅና አጠ/ስ/ሆስፒታል የክሊኒካል ትሪያል /clinical trial center/ የምርምር ማዕከል ለማስጀመር የሚያስችል አውደ ጥናት ሰኔ 29/2013 ዓ.ም በሳይንስ አምባ አዳራሽ ተካሄደ። አውደ ጥናቱ የተለያዩ የዩኒቨርሲቲው የስራ ኃላፊወች፣መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች በተገኙበት ተካሂዷል።

የመድሀኒቶች ውጤታማነት መሞከሪያ የምርምር ማዕከሉን /ክሊኒካል ትሪያል/ ለማስጀመር ሆስፒታሉ መዘግየቱን ያነሱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ፣ አሁን ላይ የማዕከሉን መዘጋጀት አድንቀዋል። አፍሪካ ውስጥ ካሉት 20 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንዱ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ቢኒያም፣ በሀገራችን ትልቅ ጉዳት በሚያስከትሉ በሽታዎች ላይ ለምሳሌ:- ወባ፣ ቲቢ፣ ካላዛርና የመሳሰሉት በሽታወች ላይ ይህን የመድሀኒቶች ውጤታማነት መሞከሪያ ማዕከል ተግባራዊ ማድረግ የተለያዩ ምርምሮችን ለመስራት ጭምር እንደሚያግዝም ም/ፕሬዚዳንቱ አክለው ገልፀዋል።

በአውደጥናቱ ስለ ክሊኒካል ትሪያል /clinical trial/ ታሪካዊ አመጣጥ፣ አስፈላጊነት እና በመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዩች ዙሪያ የህ/ጤ/ሳ/ኮ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር በሆኑት በፕ/ር ታደሰ አወቀ እና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት በዶ/ር መዝገቡ ሰላምሰው ገለጻ እና ማብራሪያ ከቀረበ በኋላ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፤ የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦችም ከተጋባዥ እንግዶች ተነስተዋል ፡፡

