የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሁለት የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከላት አራት የኤሌክትሪክ ወፍጮዎች ድጋፍ አደረገ !!
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ለካለን ብናካፍል የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ሁለቱን የኤሌክትሪክ ወፍጮዎች ድጋፍ በሚያደርጉበት ወቅት እንደተናገሩት መርጃ ማዕከሉ ትልቅ ራዕይ ይዞ እየሰራ ያለ መሆኑን በአካል በተደጋጋሚ መጥተን ተመልክተናል፤ በዚህም መሰረት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረግን ቆይተናል። ሁኖም ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተረጅዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱና ቋሚ የገቢ ምንጭ ሊኖር ስለሚገባ ዩኒቨርሲቲው እንዚህን ሁለት ወፍጮዎች ድጋፍ አድርጓል። ለዚህ ድጋፍ መገኘት ከፍተኛ ጥረት ላደረጉት የምርምርና ማሕበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ቢሮ እና የማህበራስብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል፡፡

የምርምርና ማሕበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ ጊዜያዊ ድጋፍ ማድረግ ጊዜያዊ መፍትሄን ይሰጣል እንጅ ዘላቂ ጥቅምን አያስገኝም በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የመርጃ ማዕከሉ ቋሚ የገቢ ማመንጫ እንዲሆንለት በማሰብ ይሄን ወፎጮ አቅርቧል ስለዚህ ከበሽታ ነፃ የሆኑና መስራት የሚችሉትንም በማሰራት ማዕከሉ ሊሰራ ይገባል በእኛ በኩል ካሉን የተለያዩ ረጅና አጋር አካላት ጋር በመወያዬት ድግፋችን ይቀጥላል በማለት አስረድተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የማህበራስብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሰለሞን ፈንታው በበኩላቸው የኤሌክትሪክ ወፍጮ ድጋፍ የተደረገላቸው ለካለን ብናካፍል የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል እና ለጯሂት አቡነ-ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምንዱባን መረዳጃ ማህበር ሲሆን በጎንደር ከተማ ለሚገኘው መና የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልም እያዘጋጁት ላለው የዳቦ መጋገሪያ ፕሮግራም የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የካለን ብናካፍል የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ማህበር መስራች አቶ ዳዊት አያናው እና በማዕከሉ እርዳታ የሚደረግላቸው አቶ መንግስቱ አስፋው ለተደረገላቸው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅበዋል፡፡
