የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴት መምህራን ማህበር አውደ ጥናትና ጉብኝት አካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴት መምህራን ማህበር አውደ ጥናትና ጉብኝት አካሄደ
***************************************
የዩኒቨርሲቲው የሴት መምህራን ማህበር ከተቋቋመ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ሴት መምህራን ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን በምርምርና በአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ይበልጥ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል በርካታ ስራወችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በመሆኑም በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አቅጣጫ መሰረት ከጥቅምት 27 አስከ ህዳር 4/2013 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ሊከበር የነበረውን ‘የኢትዮጵያ የሳይንስ ሳምንት’ ምክንያት በማድርግ፣ ‘የኢትዮጵያ ሴቶች በሳይንስ በኩል – በተለይም ለወጣት ሴት ተመራማሪዎች’ (Ethiopian women in science: “Lessons for young female researchers”) በሚል ርዕስ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት አጼ ቴዎድሮስ ግቢ በሚገኘው የድህረ ምረቃ አዳራሽ ህዳር 20/2013 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡
ፕሮግራሙን በንግግር ያስጀመሩት የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣ መርሀ ግብሩን በንግግር የቋጩት የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር መሰረት ካሴ፣ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሰቲው የሴት መምህራን ህብረት ፕሬዚዳንት ዶ/ር የዝቤ ካሳ፣ የዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በአውደ ጥናቱ ተሳትፈዋል፡፡ ሴት መምህራን በማንኛውም መልኩ አቅማቸውን በማሳደግ ከመማር ማስተማሩ በተጫማሪ በምርምርና በቴክኖሎጂ ስራዎች የላቀ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ም/ፕሬዚዳንቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት አሳስበዋል፡፡
በህክምናው ዘርፍ በሀገር ውስጥም ሆነ በሀገር ውጪ ባካበቱት ልምድና ባገኙት እውቀት አንቱ ከተባሉት መካከል የሚጠቀሱት የህክምና መምህር፣ ተመራማሪና የፕሮጀክቶች አስተባባሪ ወጣት እንስት ዶ/ር ረዚቃ ሞሀመድ በዕለቱ ተገኝተው ያሳለፉትን ውጣ ውረድና ለስኬት ያበቋቸውን መንገዶች ለሙያ አጋሮቻቸው በገለጻ አስረድተዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴት መምህራን ማህበር አባላት የተጣለባቸውን ሙያዊ ኃላፊነት ከመወጣት ባሻገር በበጎ ተግባር ለተሰማሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ማህበራት በተለያዩ ጊዜያት አጋርነታቸውን ያሳያሉ፡፡ ከስዓት በኋላ በነበረው መርሀ ግብር በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ጯሂት ከተማ የሚገኘው የአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ምንዱባን በጎ አድራጎት ማህበር ተጎብኝቷል፡፡ ከጉብኙቱ ባሻገር ሴት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በፈቃደኝነት ባዋጡት 52, 000/ ሀምሳ ሁለት ሺ ብር፣ 15 ኩንታል ዳጉሳና 13 ቁምጣ ፈርኖ ዱቄት ከነ ማስፈጫ ሂሳቡ በዶ/ር የዝቤና በአቶ ሰሎሞን ፋንታው በኩል ለበጎ አድራጎት ማህበሩ ድጋፍ አድርጓል፡፡
አቶ ብርሀን መልካሙ ( የአቡነ ገ/ መንፈስ ቅዱስ ምንዱባን በጎ አድራጎት ማህበር ስራ አስኪያጅ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለምንዱባን ማህበሩ ከዚህ በፊት የተለያዩ ቁሳቁስ፣ የአልባሳት፣ የምግብ፣ የእህልና የመሳሰሉ ድጋፎች ማድረጉን አውስተው በቀጣይ መሰል ድጋፎች እንዲደረግላቸው በማሳሳብ ለተደረገላቸው ሁሉ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ አመስግነዋል፡፡
**********
,
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ህዳር 21/2013 ዓ.ም






