የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሕክምና ምርመራ የጥናት ምርምር አቅምን ለማጎልበት ስልጠና እየሰጠ ነው
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተ ከ65 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረ ሲሆን፣ ሰፊ የምርምር ማዕከል ያለውና በውስጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችን በማስተናገድ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህም በአጠቃላይ አፈጻጸምና በትምህርት ጥራት ከመጀመሪያው ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ለተከታታይ 3 ዓመታት አሸናፊ በመሆን የአንደኛ ማዕረግ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ተሸላሚ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ይህ ከፍተኛ አፈጻጸም ወደፊት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የበለጠ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ የተለያዩ ክፍተቶችን በመለየት በሕክምና ምርመራ የጥናት ምርምር አቅምን ለማጎልበት ለተመረጡ 25 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ሀኪሞች ከህዳር 04-07/2012 ዓ.ም የሚቆይ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ዋና ዓላማው ከውጭ ሃገር የምርምር ውጤት ጥገኝነት በመውጣት በሃገር በቀል የምርምር ሥራ በሽታዎችን ማከም እንዲቻል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን የስልጠናው ዋና አስተባባሪ ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ ገልጸዋል፡፡
ሥልጠናውን ያዘጋጀው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ሀኪሞች ማህበር ጎንደር ቅርንጫፍና ከጎንደር ሆስፒታል ጤና ባለሙያች ማህበር በጋራ ሲሆን፣ ይህን ሥልጠና መሰረት በማድረግ በቀጣይ ምርምር የሚሰሩባቸው ዘርፎች በሥዕነ-አዕምሮ፣ በእናቶች ጤና፣ በሕፃናት ጤና፣ በቀዶጥገና እና ኢንፌክሽን፣ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑን እና ሥልጠናው ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የሚቀጥል እንደሆነ ዶ/ር ቢናኒያም አክለው ገልጸዋል፡፡
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



