
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቤተሰብ ፕሮጀክት ለ2ኛ ጊዜ የቃልኪዳን ቤተሰብ ትውውቅ አካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዲስ ለተመደቡ ተማሪዎች የቃልኪዳን ቤተሰብ ትውውቅና ትስስር ፕሮግራም ዛሬ ማለትም ሀምሌ 25/2013 ዓ.ም የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ አግማስ፣ የቀድሞው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ፕ/ር መንገሻ አድማሱ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ም/ፕሬዚዳንቶች ፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች የቃል ኪዳን ቤተሰብ ለመሆን ፍላጎት ያላቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች እና የዩኒቨርሲቲያችን የአካዳሚክ እና የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም ተማሪዎቻች በታደሙበት ተካሂዷል።
የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደዎይን በመክፈቻ ንግግራቸው ኢትዮጵያዊያን የተጋረጡባቸውን አንድነትን የሚሸረሽሩ ብዙ ፈተናዎች ለመፍታት የሚያስችሉ ስልቶችንና አሰራሮችን መቀየስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲም በተለያዩ ምክንያቶች እየተሸረሸረ የመጣውን ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ለመመለስ በአይነቱ ለየት ያለ “የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት” በሚል ስያሜ ከ2012 ዓ.ም ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ወደ ዩኒቨርሲቲያችን የሚመደቡ ተማሪዎችን በአግባብ በመቀበል ከጎንደር ከተማ ማኅበረሰብና ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የቃል ኪዳን ቤተሰብ በመምረጥ እያስተዋወቀና እያስተሳሰረ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተሰራ ያለው ተግባር ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ሊያጠናክርና ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አርዓያ እንደሆነ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ተሾመ አግማስ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም “ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመድባችሁ የመጣችሁና ዛሬ የቃል ኪዳን ቤተሰብ ትውውቅና ትስስር የምታደርጉ ተማሪዎች የአማራን ህዝብ እውነተኛ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ እና ማንነት በውል ተገንዘባችሁና አውቃችሁ ለቀሪው የሀገራችን ህዝቦች ይህንን እውነታ በማስረዳት በአማራ ህዝብ ላይ ያለውን የተዛባ አመለካከት እንደምትቀይሩና ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ከምንጊዜውም በላይ እንዲጠነክር አበክራችሁ እንደምትሰሩ ፅኑ እምነት አለኝ” በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት በጎንደር ማህበረሰብና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ጥብቅ ቤተሰባዊ ትስስር በመመስረት፤ በጎንደሬ የእንግዳ ወዳጅነትና አክባሪነት ኢትዮጵያዊነት አንድነትን በማጠናከርና ምቹ የትምህርት ጊዜ በመፍጠር የሀገርና የወገን መከታ የሚሆኑ ምሩቃንን ለማፍራት አላማው ያደረገ መሆኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ታደሰ ወ/ገብርኤል በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት በየአመቱ ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚመጡ አዳዲስ ተማሪዎች በጎንደር ከተማ ውስጥ ከሚኖሩ ነዋሪዎች ጋር ተገቢውን ፍቅርና እንክብካቤ የሚያገኙበት ብሎም ለትምህርትና ስልጠና በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ጊዜ ከጎናቸው በመሆን አስፈላጊውን ቤተሰባዊ ክትትልና ድጋፍ እንዲያገኙ መሰረት ያደረገ ፕሮጀክት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
“ዲሽታጊና” በሚለው ሙዚቃ በአጭር ጊዜ ታዋቂነትና ተወዳጅነትን ያተረፈው በሙዚቃ መልዕክቱ አብሮነትን፣ አንድነትን እንዲሁም መቻቻልን ያስተማረው ታሪኩ ጋንካሲ /ዲሽታጊና/ እንዲሁም የኢትዩጵያን አንድነት ለማስቀጠል ስለኢትዮጵያዊነት የሚመሰክሩ ሀገር ወዳድና የታሪክ አንቂ ምሁራኖች ሙክታር ኦስማን/ሙክታሮቪች ኦስማኖቫ/ እና አቶ ታየ ቦጋለ በመድረኩ ላይ በመገኘት አንድነትና መቻቻልን የሚሰብኩ ቁልፍ መልእክቶችን አስተላልፈዋል። በአሉን ታሪኩ ጋንካሲ /ዲሽታጊና/ ከፋሲል ባንድ ጋር በመሆን ሞቅ ደመቅ አድርገውት ውለዋል።
በመድረኩ በተማሪወችና በቃል ኪዳን ቤተሰባቸው መካከል የትስስርና የቤተሰብነት ቃልኪዳን የስምምነት ፊርማ ተካሒዷል፤ቤተሰባዊ ትውውቅም ተደርጓል። በተጨማሪም የአማራ ክልል መንግስት የጎርጎራ ከተማን ማስተር ፕላን እንዲያዘጋጅ በሰጠው ኃላፊነት መሠረት ላለፉት ስምንት ወራት በዩኒቨርሲቲዉ ሲሠራ ቆይቶ እና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተተችቶ የመጨረሻው ፕላንና ሰነድ በዛሬው ዕለት ለጎርጎራ ከተማ መሪ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ ለአቶ አማኑኤል ሸቁጥ ዩኒቨርሲቲው አስረክቧል። ይህን ታላቅ ኃላፊነት በሚገባ ለተወጡ የዩኒቨርሲቲያችን መምህራንና አስተባባሪዎች እንዲሁም ሙያዊ ግብዓት በመስጠት ለተባበሩ ባለድርሻ አካላት ሁሉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከጎንደር ከተማ አስተዳደርና ከከተማው ማህበረሰብ ጋር በመሆን የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክትን ተግባራዊ በማድረግ ካለፈው አመት ጀምሮ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡