የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ መምህራን በ Research Grant Writing Techniques ( በምርምር ድጎማ ማግኛ ስልቶች) ዙሪያ ልምዳቸውን አካፈሉ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ የምርምር ማዕከል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ድጎማን በማፈላለግና በማግኘት ሰፊ ልምድ ያላቸውን ዶ/ር ቢኒያም ጨቅሉንና አቶ ገበየሁ በጋሻውን በመጋበዝ በ Research Grant Writing Techniques( በምርምር ድጎማ ማግኛ ስልቶች) ያላቸውን ጥሩ ተሞክሮ ለኮሌጁ መምህራንና ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች ህዳር 25/2013ዓ/ም በአልሙኒየም ህንፃ አዳራሽ ልምዳቻን እንዲያካፍሉ አድርጓል፡፡
ፕሮግራሙን የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ውለታው መኩሪያው የከፈቱ ሲሆን፣ በንግግራቸው እንደዚህ አይነት የልምድ ልውውጦችና ስልጠናዎች መውሰድ ካለን አቅም በተጨማሪ ራስን ከወቅታዊና ከአዳዲስ አሰራሮች ጋር ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ አውስተው፣ ልምዳቸውን ለሚያካፍሉ ምሁራን ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል፡፡ወደፊትም ፕሮፌሰሮች እና ሌሎች ምሁራን ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት መሰል ፕሮግራም ማዘጋጀት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በመቀጠልም ዶ/ር ቢኒያም ጨቅሉ በ Research Grant Writing Techniques( በምርምር ድጎማ ማግኛ ስልቶች) እና ፅንሰ ሀሳቦች ዙሪያ ሰፊ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን፣ እራሳቸው ከሰሯቸውና ስኬታማ ከሆኑባቸውና ካልሆኑባቸው ምርምሮችና ባገኟቸው ግብረ-መልሶች ዙሪያ በመስኩ ያላቸውን ሰፊ ልምድ አካፍለዋል፡፡ በተጨማሪም ዶ/ር ቢኒያም ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ መሆኑ የበለጠ ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ስለሚችል መምህራንና ተመራማሪዎች በጋራ በርካታ ስራዎችን መስራት እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ በአቶ ገበየሁ በጋሻው በኩል በዘርፉ ያላቸውን ልምድ አካፍለዋል፡፡ በተሳታፊዎችም አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበው ውይይት ተካሂዷል፡፡
የኮሌጁን የምርምር ማዕከል ግቦች ለማሳካት ከሚረዱ የማስፈፀሚያ ስልቶች ውስጥ አንደኛው ፕሮግራም እንደሆነና በቀጣይ በሚዘጋጁ መሰል መድረኮችም የኮሌጁ መምህራን ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቅሰም እና ውስጣዊ የመነቃቃት ስሜትን በመፍጠር፣ ልዩ ልዩ የምርምር ድጎማ ያስገኛሉ ተብሎ ተስፋ እንደሚደረግ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡
**************************************************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙት ዳይሬክተር
ህዳር 25/2013 ዓ.ም







