የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠ/ስፔ/ሆስፒታል የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል በማዘጋጀት ህክምናውን ለመስጠት በቁሳቁስና በባለሙያ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ
ዩኒቨርሲቲው የኮቪድ-19 ህክምና መስጫ ማዕከል አዘጋጅቷል፤የህክምና አገልግሎቱን ለመስጠትም ባለሙያዎች አስፈላጊውን የጥንቃቄ ስልጠና መውሰዳቸው ተገልጧል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለህጻናት ህክምና አስቦ ያስገነባውን አዲስ ህንጻ ከወቅታዊ ችግር አንጻር ለኮሮና ህክምና መስጫ ማዕከል እንዲሆን በመወሰን አስፈላጊው የአልጋ፣የህክምና መስጫ፣ የንጽህና መጠበቂያ እና ሌሎች ቁሳቁሶች መሟላታቸውን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠ/ስፔ/ሆስፒታል ነርስ አቶ ጋሻው አስማረ ገልጸዋል፡፡ የህክምና አገልግሎቱን ለመስጠትም በተለያዩ የስራ ክፍል ለሚገኙ 810 ለሚሆኑ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን አቶ ጋሻው ገልጸዋል፡፡

በተለይ ለህክምና እና ለጤና ባለሙያዎች የተሰጠው አጭር ስልጠና ባለሙያዎቹ በህክምና መስጫ ማዕከሉ የራሳቸውንና የታካሚወችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ እንዴት ህክምና መስጠት እንዳለባቸው ግንዛቤ መፍጠር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ስልጠናው አንድ የህክምና/የጤና ባለሙያ አስፈላጊውን የጥንቃቄ ልብስ አድርጎና ህክምናውን ሰጥቶ የተጠቀመባቸውን አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዴት በተገቢው መንገድ ማስወገድ እንዳለበት የሚያሳይ ትግበራ ነው፡፡

የተዘጋጀው የህክምና ማዕከል ሶስት በሮች ያሉት ሲሆን አንደኛው በር ታካሚወች ወደ ህክምና የሚገቡበት፣ ሁለተኛው በር አገግመው የሚወጡበት፣ሶስተኛ ደግሞ የባለሙያዎች መግቢያና መውጫ በር ነው ፡፡ በማዕከሉ 320 የህሙማን አልጋዎች ተዘጋጅተዋል፡፡

የተወሰኑት አልጋዎችም የትንፈሳ ስርአትን የሚያግዙ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች /ሜካኒካል ቬንትሌተር / እና “በሴንሰር” የሚሰሩ የእጅ መታጠቢያወች ተሟልቶላቸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ምንትዋብ ጤና ጣቢያ ለኮቪድ-19 የህክምና መስጫ ማዕከል ተብሎ መመረጡ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጅ ጤና ጣቢያው ለባለሙያም ሆነ ለህሙማን ምቹ እንዳልሆነ የሚያሳይ ጥናት ቀርቦ በሆስፒታሉ ያለው ህንፃ ለህክምና መስጫ ማዕከል እንዲሆን በመወሰን አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የሆስፒታሉ አገልግሎት ጥራትና ቁጥጥር አስተባባሪ አቶ አምሳሉ ምህረቱ ግልጸዋል፡፡ ህንጻው እስከ 500 የህሙማን አልጋዎች መያዝ የሚችል ሲሆን ከስታንዳርድ አንጻርም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ህክምና መስጫ ማዕከል በሀገራችን ካሉ የተሻሉ የህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት አንዱ እንደሆነም አቶ አምሳሉ ምህረቱ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት በምዕራብ አፍሪካ ኢቦላን በተመለከተ የወሰዱት ስልጠና ላይ ያገኙት ልምድ ይህንን ማዕከል ለማዘጋጀት እንዳገዛቸው ከማዕከሉ አስተባባሪወች አንዱ የሆኑት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ነርሲንግ አሲ/ፕሮፌሰር አቶ መሀመድ ሀሰን ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



