የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ጋር ስምምነት አካሄዱ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በአመሰራረት የቆይታ ጊዜያቸው ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ሁለቱም ከ50 በላይ ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን በአቅም ግንባታ እና በአመራርነት ስልጠና ግንኙነት እንደነበራቸውም ታሪክ ወደኋላ ያስረዳናል፡፡
ሀገር ተረካቢና ሀገር ገንቢ ትውልድ በማፍራት ትኩረት አድርገው ለመስራት ሁለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ሰኔ10/2013 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሰኔት አዳራሽ ስምምነት አካሂደዋል፡፡

የስምምነቱ ዋና ዓላማ ቀጣይነት ያለው እና ውጤታማ የሆነ የአቅም ግንባታና የሥራ አመራር ሥልጠና መስጠት ሲሆን የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የፕሮግራሙ አዘጋጅ ነው፡፡
በስምምነቱ ላይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን፣የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር ጋሻው አንዳርጌ፣ የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣ የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢነስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ውብአምላክ እሸቱ እና የኢንስቲትዩቱ የቡድን አባላት፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደርበው ቀኑብህ እና የኮሌጁ የትምህርት ክፍል አስተባባሪዎች ተገኝተዋል፡፡

ተቀራራቢ እድሜ ላይ የሚገኙት የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ሁለቱም ለሀገራችን ከፍተኛ አስተዋፆዖ ያበረከቱ ቢሆንም አብሮ በመስራት ላይ ጊዜ ያላገናኛቸው ተቋማት ሆነው የቆዩ መሆናቸውን ዶ/ር አሥራት በመግቢያ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡ አሁንም ጊዜው ያልመሸ መሆኑን ጠቅሰው ለሀገራችን የሚጠቅሙ ሥራዎችን በጋራ እንሰራለን ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢነስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ውብአምላክ እሸቱ በበኩላቸው የጎንደር ዩኒቨርቲ ከኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢነስቲትዩት ጋር አብሮ ለመስረት ፈቃደኛ በመሆኑ ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅረበዋል፡፡ በመቀጠልም ኢነስቲትዩቱ በዋናነት በሲብል ሰርቫንቱ አቅም ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ መሆኑንና ይህም ከጎንደር ዩኒቨርቲ ጋር አብሮ በመስራት የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢነስቲትዩት በሚያዘጋጃቸው አንዳንድ የአቅም ግንባታና የሥራ የአመራር ሥልጠና ላይ የጎንደር ዩኒቨርቲ ተሳታፊ እንደነበር የአስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር ጋሻው አንዳርጌ አስተውሰው አሁን በሚደረገው ስምምነት ውጤት አምጭ ሥራዎችን በጋራ መስራት ይቻላል ብለዋል፡፡




