የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ለፀኃፊዎች የማነቃቂያ ስልጠና ሰጠ፡፡
ዩኒቨርሲቲያችን ከሀገር አቀፍ አልፎ በአለምአቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ ካደረጉት ሁኔታዊች መካከል የጸሀፊዎች አስተዋጽኦ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ በተለይም ባለጉዳይን በማስተናገድ ረገድ የጸሀፊዎች ሚና ወሳኝ ነው፡፡ አንድ ደንበኛ የጉዳዩ መፈጸም ብቻ ሳይሆን የሚስተናገድበት መንገድ በውስጡ ትልቅ ስሜት የመፍጠር ኃይል አለው፡፡ ከዚህም ባለፈ ጸሀፊዎች የአንድ ተቋም ገፅታ መስታዋቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም በእውቀት፣ በስነ-ምግባርና በክህሎት የዳበሩ ጸሀፊዎች የተቋምን ስራ በማሳለጥና የኃላፊውን የስራ ጫና በመቀነስ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

ይህንን መሰረት በማደረግም የዩኒቨርሲቲው የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ለፀኃፊዎች የማነቃቂያ ስልጠና የካቲት 21/2012 ዓ.ም በሀይሌ ሪዞርት ሰጥቷል፡፡ ስልጠናውን የሰጡት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስ/ም/ፕሬዚዳንት ረዳት አቶ ዳዊት ዳርጌ፣ የዩኒቨርሲቲው የሰው ሀ/ አስ/ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አስማማው፣እንዲሁም የአሜሪካን ኤምባሲ የትምህርት አስተባባሪ ወ/ሮ እየሩሳሌም ማንደፍሮ ሲሆኑ ዋና ይዘቱም በጸሀፊዎች ኃላፊነት፣ የሙያ ስነ-ምግባር፣ ተነሳሽነትና የደንበኛ አያያዝ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡

በስልጠናው ከተነሱት አንኳር ሀሳቦች መካከልም ፀሀፊዎች አስቀድመው ስራቸውን በመውደድና በማክበር እንዴት ሌላውን ባለጉዳይ በአግባቡ አክብረው ማስተናገድ እንደሚችሉ፤ እንዴት በትህትናና በእውቀት ተመስርተው ሁሉንም ባለጉዳይ በአግባቡና በእኩል አይን ማስተናገድ እንዳለባቸው ፤ደንበኛን በአግባቡ ለማስተናገድ በምግባር ፣በእውቀትና በክህሎት ራስን ማሻሻል የሚችሉበት መንገድ እና ሌሎች በርካታ ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡

ደንበኞች በተለያየ ስሜት ውስጥ ሆነው ሊመጡ ስለሚችሉ ጸሀፊዎች አስቀድመው ባለጉዳዮቹ ወደ ትክክለኛ ስሜታቸው እንዲመጡ የማድረግ ጥበብ ሊኖራቸው እንደሚገባ የዩኒቨርሲቲው አስ/ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጋሻው አንዳርጌ ለሰልጣኞች አብራርተዋል፡፡

“የአንድን ተቋም ገጽታ በመገንባት ሂደት ላይ የጥበቃና ደህንነት እንዲሁም የጸሀፊዎች ሚና ወሳኝ ነው ፣ ምክንያቱም ሁሉም ባለጉዳይ ቅድሚያ የሚያገናኘው ከእነዚህ አካላት ጋር ነው፣” ሲሉም ም/ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፤ ጸሀፊዎች የተቋሙን ሚስጥር በመጠበቅና በተለይም አዳዲስ ሃለፊዎችን በመርዳት ጉልህ እንቅስቃሴ እንዳለቸውም ገልጸዋል፡፡



