የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቤተ-መጻሕፍትና ዶክመንቴሽን አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጠ ፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቤተ-መጻሕፍትና ዶክመንቴሽን አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግባትና ቤተ-መጻህፍት ኤጄንሲ ጋር በመተባበር የቤተ-መጻሕፍት ሰራተኞችን አቅም የሚያዳብር ስልጠና ለ10 ቀናት ያህል ሰጠ፡፡
የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶ/ር ብርቁ ደሞዝ ስልጠናውን አስመልክተው እንደተናገሩት ቤተ-መጻህፍት ለተማሪዎች፣ ለመምህራን፣ ለተመራማሪዎችና ለሰራተኞች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ታላቅ ተቋም ነው፡፡ በመሆኑም የቤተ-መጻሕፍት ሰራተኞች በየወቅቱ ክህሎታቸውን ሊያዳብር የሚችል ስልጠና ሊያገኙ ይገባል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ስልጠናውን የሰጡት ከብሔራዊ ቤተ-መዛግባትና ቤተ-መጻህፍት ኤጄንሲ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ካሳ “ቤተ-መጻህፍት የእውቀት ማለማቻ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል እና የዕድሜ ልክ መማሪያ ተቋም ነው፡፡ በመሆኑም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቤተ-መጻሕፍትና ዶክመንቴሽን አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ሰራተኞችን በየጊዜው በስልጠና እንዲታገዙ ጥረት የሚያደርግ ሲሆን በዚህ ዓመትም በርካታ ሰራተኞችን ማሰልጠን ተችሏል ብለዋል፡፡

ከብሔራዊ ቤተ-መዛግባትና ቤተ-መጻህፍት ኤጄንሲ የስልጠናና የምክር አገልግሎት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ እስራኤል በዛ በበኩላቸው ስልጠናው በካታሎግ፣ በክላስፊኬሽን፣ በቤተ-መጻህፍት ስነ-ምግባር መርሆዎች እና በዶክመንቴሽን አያያዝ ዙሪያ የተሰጡ መሆኑን አስረደተዋል፡፡
ስልጠናውን ከተከታተሉት ውስጥ የአፄ ፋሲል ግቢ ቤተ-መፃሕፍት የኮምዩተር ቴክኒሻን ሰራተኛ የሆኑት ወ/ሮ መብራት ገብረሚካኤል ስልጠናው ስለ ቤተ-መፅሐፍት በቂ የሆነ ግንዛቤ የፈጠረልን ሲሆን እንዴት ሶፍትዋር መጠቀም እንደሚገባን፣ በዌብሳይታችን ላይ እንዴት ተማሪዎችን ማገዝ እንደምንችል እና በቤተ-መጻህፍት ስነ-ምግባር መርሆዎች ላይ እንዴት መጠቀም እንደሚገባን በሚገባ ግንዛቤ እንድናገኝ እገዛ አድርጎልናል ብለዋል፡፡



