የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምናና ሳይንስ ተማሪዎች ማህበር ዲፓርትመንቱን ለተቀላቀሉ አዲስ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም አዘጋጀ
የእንስሳት ህክምናና ሳይንስ ተማሪዎች ማህበር በዚህ አመት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው ቬተርናሪ ዲፓርትመንት ለገቡ ተማሪዎች ደማቅ የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ዛሬ መጋቢት 07/2012 ዓ.ም አዘጋጅቷል፡፡ በእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራሙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ ፣ የእንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፀጋው ፈንቴ እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምናና ሳይንስ ተማሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ተማሪ እንድሪያስ አለባቸው እንደገለጹልን ፣የተዘጋጀው ፕሮግራም አዲስ ተማሪዎችን ከነባሮቹ ጋር ለማስተዋወቅ እና ስለሙያው ሰፊ እውቀት ካላቸው ምሁራን የህይዎት ተሞክሮ እንዲቀስሙ ታስቦ ነው፡፡

ስለሆነም ተማሪዎች ከፈለጉት አላማ ለመድረስ ጥረት ከማድረግም በተጨማሪ ህግና ስርዓት አክብረው፣ እርስ በርስ ተዋደውና ተረዳድተው ሊማሩ እንደሚገባ ፕ/ር መርሻ ጫኔ መክረዋል፡፡ ም/ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም በወቅቱ ከተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ራሳቸውን ከመጠበቅ አልፎው ጓደኞቻቸውንና ህብረተሰቡን የመጠበቅ ሀላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በዚህ ፕሮግራም በተማሪዎች የተዘጋጁ ልዩ ልዩ የጨዋታና የጥያቄና መልስ ውድድሮች ተካሂደዋል፡፡ ውድድሮች ከፉክክር ይልቅ በወቅታዊ ጉዳዮች በተለይም ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ላይ ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ እያዝናኑ የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ በውድድሮቹ አሸናፊ ለሆኑ እንዲሁም በኮሌጁ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የቬተርናሪ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



