የጓሮ አትክልት አመራረት እና አመጋገብ ስልጠና ተሰጠ
የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የጓሮ አትክልት አመራረት እና አመጋገብ ከጎንደር ዙሪያ እና ከጎንደር ከተማ ለተመረጡ 40 ለሚሆኑ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮች እና የመጀመሪያ ደረጃ ርዕሰ – መምህራን ስልጠናው በቀን 18/04/2012 ዓ.ም በሌጁ አዳራሽ ተሰጥቷል።

የኮሌጅ ም/ዲን ዶ/ር አስማማው አለሙ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ አትክልትና ፍራፍሬ አመራረት እና አመጋገብ ጋር በተያያዘ ከKDP (Kosoye Development Program) ማለትም በኮሶየ ልማት ፕሮግራም ከ10 ዓመት በላይ ያካበተው የረጅም ጊዜ ልምድ እንዳለው አውስተው ይህው ስራም በአማራ ክልል በሚገኙ ወደ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች ልምዱን የማስፋት ስራ ተሰርቷል ብለዋል። በዚህ ረገድ የሆርቲካልቸር ትምህርት ክፍል ምስጋና እንደሚገባው የገለፁት ም/ዲኑ ትምህርት ክፍሉ ይህን ልምድ በአካባቢያችን በታች ጠዳ፣ በላይ ጠዳ እንዲሁም በደምቢያ ለማስፋፋት የያዘው እቅድ ውጤት እንደሚያፈራ የዚህ ስልጠና ተሳታፊዎች ስብጥር አመላካች ነው ብለዋል። የስልጠናው ተሳታፊ ርዕሰ መምህራን እንዲሁም አርሶ አደሮች ከዚህ ስልጠና ያገኙትን ልምድ ለሌሎች መምህራን፣ ተማሪዎች እና አርሶ አደሮች እንደሚያጋሩ እና እራሳቸውም የጓሮ አትክልትን በማምረት እና በመመገብ ሞዴል እንደሚሆኑ ያላቸውን ተስፋ በንግራቸው አውስተዋል።

የኮሌጁ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ እና የስልጠና ፕሮጀክቱ አባል አቶ ጥሩ ተስፋ በበኩላቸው ይህ ስልጠና ያለውን ልምድ ለማስፋት እናም የአመጋገብ ልማዳችን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት የሚያሰፋ መሆኑን ገልፀው ስልጠናው በትንሽ መሬት ላይ ማምረት የምንችላቸውን አትክልት እና ፍራፍሬ በተግባር የምናስተዋውቅበት በመሆኑ እና የማህበረሰባችን ችግር የሆነው የአመጋገብ ዘዴን በማሻሻል ጤንነቱ የተጠበቀ አምራች የሆነ ዜጋ እንዲኖር ያግዛል ብለዋል።

የጓሮ አትክልት አመራረት እና አመጋገብ ስልጠና የሰጡት አቶ ፋንታሁን አስራት በበኩላቸው በአጠቃላይ የምግብ ዋስትና ችግር የሀገር ጉዳይ አጠቃላይም የዓለም ችግር እንደሆነ ገልፀው “እኛ እንደ ባለሙያ የሀገራችን እና የአካባቢያችን ሁኔታ ስንገመግም በአማራ ክልል የምግብ ዋስትና፣ የመቀጨጭ እና የመቀንጨር ችግር ስርጭቱ ወደ 52% ገደማ እንደሆነ በተለያዩ ሪፖርቶች በመገንዘባችን ወደዚህ ስልጠና እንድንገባ ምክንያት ሆኗል” ብለዋል። አቶ ፋንታሁን እንደገለፁት የምግብ ዋስትናን ችግር ለመቅረፍ አትክልት እና ፍራፍሬ በፍጥነት የሚደርሱ በመሆናቸው የምግብ አቅርቦትን ለማስፋት እንደዚህ ያሉ ስልጠናዎች አስፈላጊ ናቸው ብለዋል። በመሆንም ይህ ስልጠና የሚያተኩረው የአመራረት እና የአመጋገብ ብቻ ሳይሆን ድህረ ምርት አያያዝ ላይ በመሆኑ ስለሚደረጉ ጥንቃቄዎች በማስገንዘብ በአያያዝ ጉድለት የሚበላሹ አትክልት እና ፍራፍሬዎች ሳይበላሹ ማቆየት እና ለምግብነት እንዲውሉ ለሚደረገው ጥረት ግንዛቤ ያስጨብጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ አትክልት እና ፍራፍሬዎች በቀላሉ የሚበላሹ ከመሆናቸው የተነሳ ከ40-50% የሚሆነው ምርት እንደሚባክን ባለሙያው አውስተው በአጠቃላይ ስልጠናው ከማሳ እስከ ገበታ ያለውን ሂደት ያስገነዝባል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይም የስነ ምግብ ስልጠና የሰጡት አቶ አሸተ ተገኘ እንደ ማህበረሰብ የአመጋገብ ልማዳችን በእጅጉ ማሻሻል እንዳለብን፣ ለሰውነት እድገት የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮች የያዙ ምግቦችን እና በተለይ ለህፃናት እንዲሁም ለሚያጠቡ እና ለነፍሰጡር እናቶች የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ምንጭ የሆኑ ብዙ ወጭና ጉልበት የማይጠይቁ በመሆኑ አትክልት እና ፍራፍሬ ማምረት እና በተመጣጠነ ሁኔታ መመገብ አስፈላጊ እንደሆነ ለሰልጣኞች መክረዋል። ይህን በማድረግም የሰውነታችን የበሽታ መከላከል አቅም መገንባት፣ ከህመም ለመፈወስ፣ የአእምሮና የጉልበት ጥንካሬ እና በስራ ቀልጣፋ እና ንቁ መሆን እንችላለን ብለዋል።
የጓሮ አትክልትን ለማምረት የሚያግዙ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት፣ አጠቃቀም እንዲሁም የጓሮ አትክልትን ከነፍሳት፣ ከተባይ እና በሽታ እንዴት መከላክል እንደሚቻል የህልዮት ስልጠናውን አቶ ደሞዝ ኪዳኔ የሰጡ ሲሆን የተግባር ምልከታ እና ገለፃ ደግሞ አቶ ይላቅ መለሰ እና ዶ/ር አሰፋ ስንታየሁ በኮሌዱ ሰርቶ ማሳያ በጋራ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም በዚህ ስልጠና ከሚሳተፉ ባለሙያዎች ጋር መልካም ግንኙነት
በመፍጠር እና ውጤታማ የአትክልት እና ፍራፍሬ ዘሮችን በማቅረብ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማስፋት ስራ እንደሚሰራ የኮሌጁ ም/ዲን ዶ/ር አስማማው አለሙ ጠቁመዋል፡፡
||የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት||



