የጓሮ አትክልት አጠቃቀም አውደ ጥናት ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ አርሶ አደሩ ያለውን ትንሽ ጓሮ ተጠቅሞ የጓሮ አትክልትን አምርቶ እንዲመገብ ለማድረግ በተለያዩ ወረዳዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንና የልማት ጣቢያ ሰራተኞች፣ የግብርና ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜያት የየግንዛቤ ማሰጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠትና የጓሮ አትክልት ዘሮችን በማሰራጨት በርካታ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ሰኔ 18/2013 ዓ.ም በምዕራብ ደምቢያ ወረዳ አብርጅሃ ቀበሌ ስለጓሮ አትክልት አጠቃቀም በተካሄደው አውደ ጥናት በፕሮጀክት ተጠቃሚ የሆኑ ትምህርት ቤቶች፣ አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ የልማት ጣቢያ ሰራተኞችና የአብርጅሃ ቀበሌ የገጠር ራስ አገዝ ሴቶች ማህበር አባላት የተሳተፉ ሲሆን የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ካሃሊ ጀንበሬ፣ የምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለምነው አሰፋ የኮሌጁ ማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ በየነ ደርሶ፣ የገጠር ራስ አገዝ ሴቶች ማህበር አስተባባሪ አቶ ከፋለ እንየው የኮሌጁ መምህራንና ሌሎች ተሳታፊ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በመርሀ-ግብሩ መክፈቻ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ካሃሊ ጀንበሬ፣ የአመጋገብ ስርዓታችንን በማስተካከል አካላዊ ብቻ ሳይሆን አዕምሯዊ ብቃት ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር ተሳታፊዎች ይህንን ፕሮጀክት ሊያሰፉና ሊያስቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡ በግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የሆርቲ ካልቸር መምህርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ ፈንታሁን አስራት በስነ ምግብ ዙሪ ለታዳሚው ገለፃ አድርገዋል፡፡ በመቀጠልም የአብርጅሀ ቀበሌ የገጠር ራስ አገዝ ሴቶች ማህበር አባላት ያመረቱትን የጓሮ አትክልት ምገብ አዘገጃጀት በተግባር በማሳየት ለተሳታፊዎች የምሳ ግብዣ አድርገዋል፡፡

በመጨረሻም ቀጣይ አቅጣጫዎች ተቀምጠው ውይይት ከተደረገ በኋላ በመ/ር ደረጃው አስረስ እና በመ/ር ሀና ግዛው አማካኝነት የጓሮ አትክልት ዘር በማሰራጨት መርሀግብሩ ተጠናቋል፡፡



