የጤናማ እናትነት ወርን #የእናትን ጤና መጠበቅ ቤተሰብ እና ሀገርን መታደግ ነው$ በሚል መሪ ቃል ተከበረ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚድዋይፈሪ ትምህርት ቤት ከኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ጋር በመተባበር የጤናማ እናትነት ወርን #የእናትን ጤና መጠበቅ ቤተሰብ እና ሀገርን መታደግ ነው$ በሚል መሪ ቃል የካቲት 6/2012ዓ/ም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሳይንስ አምባ አዳራሸ አከበረ፡፡

በዕለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አካዳሚክ ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ፣ የጤና ሚኒሰቴር የእናቶችና ህፃናት እንዲሁም የስርዓተ ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም፣ ከአማራ ብሄራዊ ክልል ጤና ቢሮ የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አበባው ገበየሁ ፣ ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ፣ ከኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር አቶ የሽጥላ ተስፋዬ፣ የሚድዋይፈሪ ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ ምህረቱ ሞላ እና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

በፕሮግራሙ የኮሌጁ አካዳሚክ ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም በእናቶችና ህፃናት ጤና ዙሪያ በሀገር አቀፍ እና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እየተሰራ ያለውን አበረታች የሆነ ስራ አድንቀዋል፡፡

በጤና ሚኒሰቴር የእናቶችና ህፃናት እንዲሁም የስርዓተ ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሯ ዶ/ር መሰረት ዘላለም ደግሞ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በንግራቸውም ኢትዮጵያ የሴቶችና የህፃናትን ጤና ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ እርምጃዎችን በመውሰድ የእናቶችና የህፃናት ጤናን በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል መቻሉን ገልፀዋል፡፡ ለዚህ ውጤት መሳካት ደግሞ እንደዋነኛ አስተዋእፆ መነሳት ካለበት አንዱ የእናቶችና የህፃናት ጤናን በመጠበቅ ረገድ በፕሮግራም ደረጃ ማስቀመጥ በመቻሉና በየደረጃው ከክልል እስከ ማህበረሰቡ ድረስ በቅንጅት መስራት መቻሉ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር መሰረት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የጤናማ እናትነት ወር #እናት የቤተሰብና የሀገር ምሰሶ ናት $በሚል መሪ ቃል እየተከበረ እንደሚገኝና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበርም ወሩን በዚህ መንገድ ማክበር መቻላቸውን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በራሳቸው ስም ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል፡፡

በመቀጠልም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም በእናቶች ጤና አጠባበቅ አገልግሎት ዙሪያ ያሉ መልካም አጋጣሚዎች እና ተግዳሮቶች በሚል የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በመጨረሻም የጎንደር ፖሊ ክሊኒክን ጤና ጣቢያን በመጎብኘት ሰፊ ውይይት ተካሂዶ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡



