ደቂቅ አካላትን (የተስቦ ትል) በመጠቀም የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት ስልጠና ተሰጠ
የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር በጠዳ አካባቢ ለተመረጡ 40 አርሶ አደሮች እና 6 የግብርና ባለሙያዎች ደቂቅ አካላትን በመጠቀም የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት የካቲት 12/2012 ዓ.ም በኮሌጁ አዳራሽ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ከሀሌ ጀምበር በመክፈቻ ንግግራቸው “የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ከተመሰረተ ወደ 10 ዓመት እየሆነው ነው፡፡ ስለዚህ ዋና ስራው መማር ማስተማር ቢሆንም የአካባቢውን ህብረተሰብ በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች እየሰራን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቴክኖሎጂ ሽግግር የአካባቢውን ማህበረሰብ እንዲጠቀም የሚያግዝ ስራ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ይህ ስልጠና ተዘጋጅቷል” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም “የዛሬው ስልጠና በብዙ አካባቢዎች ለምሳሌ በዳባት ወረዳ ተፈትኖ ውጤታማ የሆነ እና በቀላል ወጪ አፈርን ማልማት የሚችል ቴክኖሎጂ በመሆኑ ስልጠናው ለአካባቢው እጅግ አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡ “እኛ ጠርተናችሁ ብቻ ሳይሆን እናንተም በተደራጀ መልኩ ጠይቃችሁ የአካባቢውን ችግር የሚፈቱ በተለያዩ ጉዳዮች የምትፈልጉትን የቴክኖሎጅ ሽግግር ስልጠናዎች መወሰድ ይኖርባችኃል” ሲሉ ለሰልጣኞች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በተመሳሳይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ውለታው መኩሪያ በበኩላቸው” በሀገራችን የአየር ንብረት እየተቀየረ፣ ሙቀት እየጨመረ ዝናብ እያጠረ፣ ህዝብ እየጨመረ ነው፤ በተቃራኒው ደግሞ የአፈር ለምነት እየቀነሰ፣ አካባቢ እየተበከለ እና ጤናችንም እየታወከ በመሆኑ እኛም እናንተም ዝምብለን መቀመጥ ሳይሆን አማራጭ መፍትሄ መፈለግ እና መፍጠር አለብን” ብለዋል፡፡ በመሆኑም ይህ ስልጠና በተፈጥሮ ዘዴ አፈርን የማልማት ቴክኖሎጂን የሚያስተዋውቅ በመሆኑ ለአካባቢው ማህረሰብ ጠቃሚ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ሀይሉ ክንዴ የተፈጥሮን ማዳባሪያ ምንነት፣ አዘገጃጀት እና የሚያስገኘውን ጠቀሜታ እንዲሁም የተስቦ ትልን በመጠቀም የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዴት እንደሚዘጋጅ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡
የሕዝብ እና ዓለም አቀፍግንኙነት ዳይሬክቶሬት



