ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ 19 ታካሚዎችን መረጃ ለመከታተል የሚያስችል አዲስ መተግበሪያ /Software Application / አዘጋጀ
በአለም ዙሪያ ያሉ ምሁራን የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ከክትባት እስከ መድኃኒት ይሆናል ያሉትን ለማግኘት ከተፍጨረጨሩ ወራት አልፈዋል፡፡ይሁን እንጅ ጥረታቸው አጥጋቢ ፍሬ አላፈራም፤ ሰለሆነም ፍቱን መድኃኒት ይሆናል ያሉት አንድ ነገር ብቻ ነው-አስቀድሞ መከላከል፡፡

አስቀድሞ ለመከላከል ደግሞ ዋናው ጉዳይ ከአካለዊ መቀራራብና ከንክኪ መራቅ ነው፡፡ በተለይ በሆስፒታል አካባቢዎች የሚፈጠረውን አካላዊ መቀራረብ ስናይ ደግሞ የበሽታውን ስጋት ከፍ ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም ይህን አካላዊ መቀራረብ ያስቀራል ያሉትን ዘመናዊ የመረጃ ስርዓት መተግበሪያ/ Software Application/ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህከምና እና የኢንፎርማቲክስ ምሁራን አዘጋጀተዋል፡፡ አፕሊኬሽኑ ወይም መተግበሪያው የቀረበው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች ምሁራን በተገኙበት በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ድህረምረቃ አዳራሽ ሚያዚያ 07/2012 ዓ.ም ነው፡፡

መተግበሪያውን ያቀረቡት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ሳይንስ መምህርና የጤና ላቦራቶሪ የቴክኒክ ረዳት መምህር ፈድሉ ኑርሁሴን፣ አፕሊኬሽኑ የኮምፒዩተር ሶፍትዌር ሲሆን የኮቪድ -19 አጠቃላይ መረጃ አያያዝ ስርአትን ቀላልና ተደራሽ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረውም ሆነ መታመማቸው ተረጋግጦ በለይቶ ማቆያ የህክምና ክትትል ያሉ ታካዎችን አጠቃላይ መረጃ ከግለሰቦቹ የጉዞ ታሪክ ጀምሮ እስከ ላቦራቶሪና የህክምና ውጤት እንደሚያሳይም አቅራቢው አብራርተዋል፡፡

እንደ መምህር ፈድሉ ገለጻም፣ ይህን ተግባራዊ ለማድረግም በሆስፒታሉ ኔትወርክ ተዘርግቷል፡፡ይህንን መረጃ የማየትና የመጠቀም ስልጣን የሚኖራቸውም ፕሪቪሌጅ የተሰጣቸው የህክምና ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም የታካሚ ግለሰቦች የህከምና ምስጢር ከሀኪሞቻቸው ውጭ ሌላ አካል የማየት ስልጣን /ፕሪቪሌጅ /የለውም፡፡ አዲሱ መተግበሪያ የነበረውን የወረቀት አሰራር ከማዘመንም በላይ በሰዎች መካከል የሚፈጠረውን አካላዊ መቀራረብና ንክኪ በማስቀረት የኮሮናን ወረርኝ በመከላከል ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡

የኮምፒዩተር ሶፍትዌሩ በትብብር መሰራቱ እውቀትን ከመጋራት ባሻገር መተግበሪያውን ዘላቂና አሰተማማኝ እንደሚያደርገው በፕሮግራሙ የተገኙ ከፍተኛ አመራሮች ገልጸዋል፡፡የአንዲት ሀገር ትልቁ ሀብት በእውቀትና በተግባር ትርጉም ያለው ስራ የሚያሳይ የሰው ሀብት መኖር መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ተናግረዋል፡፡ “ከሌሎች ሀገራት ተጽእኖ ነጻ በመሆን የራሳችንን ስርአት መዘርጋት ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነን ፤ይህ ደግሞ ጥሩ ጀማሮ ነው፣” ሲሉም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ካሳሁን አለሙ ፣ መተግበሪያውን ለመስራት የተሳተፉትን የተለያዩ የሄልዝ ኢንፎርማቲክስ፣የኤፒዲሞሎጂ፣ የህክምና እና የኮምፒዩተር ሳይንስ ምሁራን አመስግነው፣ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ተቋሙ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከሚመለከታቸው የዞንና የከተማው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
መጋቢት 08/2012 ዓ.ም



