ፕሮፌሰር ጋሻው አንዳርጌ
ለሙሉ ፕሬፌሰርነት ማዕረግ ስለበቁ እንኳን ደስ አለዎት!
“አስተውሎ የሚራመድ ረጅም ርቀት ይጓዛል” የሚለው መርህ ብዙ ትምህርት ቤቶች ሰንደቅ ዓላማ መስቀያ ሰገነት ስር ተጽፎ አንብበን ይሆናል፡፡ ጥቂቶች ደግሞ በተግባር አሳይተውናል፡፡ ከጥቂቶቹ ውስጥ አንዱ ፕሮፌሰር ጋሻው አንዳርጌ ናቸው፡፡በፈተና ብዛት ያልወደቁ፣እንቅፋት አደናቅፎ ያልጣላቸው፣ችግር ጎትቶ ያላጎበጣቸው፣መንፈሰ ጽኑና ቁርጠኛ ምሁር መሆናቸውን በአደባባይ አስመስክረዋል፡፡

ፕሮፌሰር ጋሻው የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአካባቢ ጤና ሳይንስ (Environmental Health Science) አጥንተው በ1984 ዓ.ም በዲፕሎማ ተመረቁ፡፡ መመረቅን ከጎንደር የጀመሩት ሩቅ ዓላሚ፣ትጉህ መንገደኛ በ1993 ዓ.ም ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢ ሳይንስ (Environmental Science) የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ሰውዬው እንደ በረሃ ችግኝ እውቀት ቶሎ ቶሎ ይጠማቸዋል፡፡ማንበብ ልማዳቸው፣ መመርመር ባህሪያቸው ነው፡፡አዳዲስ ነገሮችን የማወቅ ጉጉት አላቸው፡፡በመሆኑም ብዙ ሳይቆዩ የጤና አመራርና ምጣኔ (Health Management and Health Economics) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በ1998 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀበሉ፡፡ በእውቀት እየዳበሩ፣በአመለካከት እየበሰሉ ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ከዛሬ በላይ ለነገ ስንቅ ቋጠሩ፡፡ከትናንቱ ትዝታ የነገው ተስፋ ወኔ ሆናቸው፡፡ መማር ለእርሳቸው እንደሚበሉት ምግብ እንደሚጎነጩት ውሃ ነው፡፡ ሳይውሉ ሳያድሩ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በህብረተሰብና ህጻናት ጤና (Public and Child Health) ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ሰሩ፡፡ እረፍት የለሹ ሰው በተጓዳኝ የወሰዷቸው አጫጭር ስልጠናዎች እና የተሳተፉባቸው ዓለም ዓቀፍ ዓውደ ጥናቶች በርካታ በመሆናቸው ለመዘርዘር ጊዜና ቦታ አይበቃንም፡፡ በጥቅሉ ግን መማር፣ማስተማር፣መመራመር እና ወገንን ማገልገል መደበኛ ስራዎቻቸው ናቸው፡፡አይደክሙም አይሰለቹም፡፡ በቃኝ በቅቻለሁ አይሉም፡፡
ፕሮፌሰር ጋሻው አንዳርጌ ላለፉት 26 ዓመታት የቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ ተማሪዎችን አስተምረዋል፣አማክረዋል፡፡ በ19 ዓመት የተመራማሪነት ዘመናቸው ወደ 90 የሚጠጉ ጥራታቸው የተረጋገጠና ለጤናው ዘርፍ ማጣቀሻነት የሚያገልግሉ እንዲሁም የፖሊሲ አቅጣጫ የሚጠቁሙ ምርምሮችን በታዋቂና ዓለም ዓቀፍ ጆርናሎች አሳትመዋል፡፡ ስድስት ማስተማሪያ መጽሐፎችን በመፃፍ ለተጠቃሚዎች አበርክተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ጋሻው አንዳርጌ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች አገልግለዋል፡፡አሁንም በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ የህብረተሰብ ጤና ት/ቤት ኃላፊ (በኋላ ዳይሬክተር)፣ የህክምናና ሳይንስ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ምርምርና ህትመት ባለሙያ (officer)፣የሆስፒታል አስተዳደር ፣ የዳባት ምርምር ማዕከል አስተባበሪ እንዲሁም የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አካዳሚክ ዳይሬክተር ሆነው ኃላፊነታቸውን በብቃት ተወጥተዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ምክትል ፕሬዚደንት የሆኑት ፕሮፌሰር ጋሻው አንዳርጌ እውነትና እምነትን ይዘው በቁርጠኝነት እየመሩ ይገኛሉ፡፡ ለከፋው ደራሽ፣ከመስመር ለወጣ አስታጋሽ ናቸው፡፡ ቀና ልቦና የታደሉ፣በአመራር የተካኑ፣ለአመኑበት የማያፈገፍጉ እና ሃቅ መርሃቸው እንደሆነ በደንብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድም ትናንት ግንቦት 22/2012 ዓ.ም በ “Microsoft Teams” ባካሄደው ስብሰባ በሚመለከታቸው የትምህርት ክፍሎች ተመርመሮ፣ በየኮሌጆቹ አካዳሚክ ጉባዔዎች ተፈትሾ፣ በውስጥና በውጭ ገምጋሚዎች ተረጋግጦ፣ በዩኒቨርስቲው ሴኔት ታይቶ እና ይሁንታ አግኝቶ የቀረበለትን የዶ/ር ጋሻው አንዳርጌ መረጃ ተመልክቶ ሙሉ ፕሮፌሰር እንዲሆኑ አፅድቋል፡፡
ፕሮፌሰር ጋሻው አንዳርጌ በድጋሜ እንኳን ደስ አለዎት እያልን ካለፈው በላይ የሚመጣው አግልግሎትዎ የበዛ እንዲሆን እንመኛለን፡፡
ህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ግንቦት 23/2012 ዓ.ም



