122ኛው የአድዋ ድል በዓል በድምቀት ተከበረ
የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝብ የኩራት ምንጭ፣ የድል ምሳሌ እና የአንድነት ምልክት የሆነው የአድዋ ድል በዓል የካቲት 22/2010 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብዕ ኮሌጅ አዘጋጅነት በሳይንስ አንባ አዳራሽ በድምቀት ተከበረ፡፡
በበዓሉ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ ሰራተኞችና ተማሪዎች እንዲሁም የሰሜን ጎንደር ዞን ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
[widgetkit id=8507]
ፕሮግራሙ በአድዋ ጦርነት ለተሰው ጀግኖች አርበኞች በተደረገ የህሊና ፀሎት የተጀመረ ሲሆን፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ካሳሁን ተገኝ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ዶ/ር አስራት አፀደወይን መርሀ ግብሩን በንግግር ሲከፍቱ፣ ‹‹የአድዋ ድል የማንነታችን መገለጫ ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ትግል አይነተኛ ሚና የተጫወተ ድል በመሆኑ ልንኮራበትና ልንዘክረው ይገባል›› ብለዋል፡፡ ዶ/ር አስራት አያይዘውም ቀጣዩ ትውልድም የአባቶቹን አኩሪ ታሪክ ጠብቆ እንዲቆይ የማስገንዘብና የማስተላለፍ ታሪካዊና ሀገራዊ ሀላፊነት አለብን ብለዋል፡፡
ዝግጅቱም በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች የደመቀ ሲሆን፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ትምህርት ክፍል መምህራንና ተማሪዎች ታዳሚያንን በተለያዩ ጣዕመ ዜማዎች በማዝናናት፣ የቲያትር ጥበባት ትምሀርት ክፍል መምህራንና ተማሪዎችም እቴጌ ጣይቱ የተሰኘ ቅንጭብ ታሪካዊ ቲያትር በማቅረብ፣ ታዳሚውን በማዝናናትና በማስተማር ታሪክን ዘክረዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ከአዝናኝ ዝግጅቶች በተጨማሪም በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር በሆኑት በዶ/ር ፈንታሁን አየለ ‹‹ በአድዋ ዘመቻ የሴቶች ተሳትፎ›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል›፡፡ በጥናታዊ ፅሁፉም ምግብ ማዘጋጀትና በማቅረብ፣ ውሀ በማቀበል፣ የቆሰሉትን በባህላዊ መድሀኒት በማከም፣ በጦርነቱ የተሰዉትን በመቅበር እና ከተሰውት ወታደሮች እጅ መሳሪያ በማንሳት፣ ጠላትን በመሰለልና መረጃ በማምጣት እንዲሁም በግንባር በመዋጋት ጭምር ሴቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልፀዋል፡፡ ፅሁፉን መነሻ በማድረግም ከታዳሚያን ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
በመጨረሻም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሉቀን አዳነ ይህንን የኩራታችን ምንጭ የሆነ የድል በዓል እንደዚህ በአማረ መልኩ ለአዘጋጀውና ለዘከረው የማህበራዊና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ በተለይ ደግሞ በዓሉን በማዘጋጀት የአንበሳውን ድርሻ ለያዙት የታሪክና ቅርስ አስተዳዳር ትምህርት ክፍል፣ ቲያትር ጥበባት ጥምህርት ክፍል፣ ለሙዚቃ ትምህርት ክፍልና ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡ መሰረት አለምነህ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



