13ኛው የአማራ ክልል የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ፎረም የምክክር ጉባኤ ተካሄደ
13ኛው የአማራ ክልል የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም የምክክር ጉባኤ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከሀምሌ 16-17/2008 ዓ/ም የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በጎጃም የባህል ሙዚቃ ባንድ ታጅቦ በድምቀት ተካሂዷል፡፡
በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ እንኳን ለ13ኛው የአማራ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጉባኤ አደረሳችሁ በማለት ለተሳታፊዎች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመቀጠልም በአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የሚካሄደው የጋራ ፎረም ከተጀመረ አንስቶ ዩኒቨርሲቲዎች በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ችግር ፈቺ እንቅስቃሴዎችን እያካሄዱ ይገኛሉ በተለይም በዚህ አመት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎቻችን ሰላምን ለማስፈን የነበረው እንቅስቃሴ ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል ካሉ በኋላ ይህን ጅምር የጋራ እንቅስቃሴ ዳር ለማድረስ በቀጣይ የ2009ዓ/ም የተሻለ ስራ ሰርቶ ለመገኘት ተግተን ልንሰራ ይገባል በማለት ጉባኤውን በይፋ ከፍተዋል፡፡

ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ የደብረ ማርቆስ የኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ
በጉባኤው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እና የአማራ ክልል የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጉባኤ ሰብሳቢ ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ 7ቱም ዩኒቨርሲቲዎች ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ አድርገው በሪፖርቱ ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን ከተነሱት ሃሳቦች መካከል ጥቂቶቹ ፡-ሪፖርት ሲቀርብ ከተለመደው አቀራረብ ወጣ ብሎ በአንድ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ና ጥናታዊ ሆኖ ቢቀርብ፣ የትምህርት ፕሮግራሞች ሲቀረጹ አካባቢን መሰረት ያደረገ ቢሆን፣ ዩኒቨርሲቲዎች ባላቸው ከፍተኛ ትስስር ልክ የጋራ ውጤታቸው ጎልቶ ሊታይ ይገባል፣የመምህራንና ተማሪዎች ገንኙነት ሳይንስን መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል የሚሉ የማስተካከያ የጋራ ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡

ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ፎረም ሰብሳቢ ጉባኤውን ሲመሩ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዓመቱ ውስጥ የተከናወኑ አጠቃላይ ተግባራትን በምስል በተደገፈ መልኩ በዝርዝር በቀረበው ሪፖርት የስማርት ቦርድ ክላስ፣ ሰኪዩር ካሜራ፣ ቴሌ ሜድስን እና አጠቃላይ የግንባታ ስራዎቹ ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተምሳሌት እንደሆነ በተሳታፊዎች ተገልጿል ፡፡
በጉባኤው ላይ የዩኒቨርሲቲዎችን የጋራ እንቅስቃሴ በሚያሳዩ በመርዛማ እፅዋት የተበከሉ ሃይቆችን በተመለከተ እና የህዋ ሳይንስ ምርምርን በማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ቀርቧል፡፡የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲና የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ተሞክሯቸውንም ያቀረቡ ሲሆን ክብርት አምባሳደር ዶ/ር ገነት ዘውዴ ባህለ ብዝሃነት /multi culturalism/ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ፅሁፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል:: በመጨረሻም የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የስራ ጉብኝት አካሂዶ ጉባኤው በሠላም ተጠናቋል፡፡
ዘጋቢ ፡- በላይ መስፍን



