26ኛው አመታዊ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት እና ቴክኖሎጅ ሽግግር ጉባኤ ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ 26ኛው አመታዊ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጅ የሽግግር ጉባኤ ‹ሳይንስና ቴክኖሎጅ ለኢትዮጲያ ህዳሴ› በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ከተለያየ ዩኒቨርሲቲ የመጡ መምህራን እና ጥናት አቅራቢወች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ፣ አርሶ አደሮች፣የወረዳ አመራሮችና ከሀገር ውጭ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ሙሁራን በተገኙበት ከሰኔ 17-18/2008 ዓ.ም በሳይንስ አምባ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጲያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በ4ተኛ ዙር ባዘጋጀው አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት የ1ኛ ደረጃ ዋንጫ ማግኘቱን ለታዳሚው ካበሰሩ በኋላ ዩኒቨርሲቲው የተመሰረተበትን አላማ ሳይረሳ አሁንም በማህበረሰብ አገልግሎት ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑንና በዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች ትምህርት ቤቶች፣ እና ተቋማት በርከት ያሉ ጥናትና ምርምሮች እየተሰሩና መልሰው ለማህበረሰቡ አገልግሎት መዋሉ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የሚያደርገውን ጉዞ እያፈጠነ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ የጉባኤው ተሳታፊወች በከፊል
ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታከለ ታደሰ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በሀገራችን ካሉ ዩኒቨርሲቲወች ግንባር ቀደም ችግር ፈች ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት አንድ ሀገር ለመገንባት ስለሆነ ሁሉም የውይይቱ ተሳታፊ የጋራ ራዕይና የባለቤትነት ስሜት ኖሮን በጋራ ለመስራት ሀላፊነት ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡

የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታከለ ታደሰ የጉባኤው ተሳታፊወች በከፊል
በጉባኤው በርከት ያሉ የጥናትና ምርምር ፁሁፎች የቀረቡ ሲሆን በዶ/ር ተፈራ ዋልዋ የቀረበው የህዋ ሳይንስ ጥናትና ውጤቶች አንዱ ሲሆን በተጨማሪም በተያዘው አመት በዩኒቨርሲቲው የተከናወኑ የማህበረሰብ አገልግሎትና የምርምር ስራወች ለማህበረሰቡ ቀርበዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል አገልግሎት ዋናዋና ክንውኖች፣ የነፃ የህግ አገልግሎት ማእከላትና የማህበረሰብ አገልግሎት፣ በግብርና ምርምር ማእከላት የተሰሩ የምርምር ስራ ውጤቶችና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችና በቱሪዝም እና ባህል ሴክተር የተሰሩ የማህበረሰብ አገልገሎት ስራዎችና የማህበረሰቡን ሀብት በመጠቀም ልማትን ማምጣት መቻሉን ያሳዩ ፕሮጀክቶች የቀረቡ ሲሆን ጹህፎቹ ከቀረቡ በኋላም በማህበረሰቡ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በጉባኤው የቀረቡ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና ሳይንስና ቴክኖሎጅ ውጤት ስራዎች ለማህበረሰቡ እና ለወረዳ አመራሮች በአማርኛ ቋንቋ መቅረቡ ውይይቱ ውጤታማ እንዲሆንና ውይይቶችም ለወደፊት ለሚደረጉ የማህበረሰብ አገልገሎትና የምርምር ስራወች ግብአት እንደሚሆኑ አመላካች ስራ ከመሆናቸው በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በበርካታ የጥናትና ምርምር ማቅረቢያ መድረኮች የሚታየውን የታዳሚ ድርቅ እንደሚቀርፍ ያሰየ ፋናወጊ ስራ በመሆኑ ሌሎች ዩኒቨርሲቲወችም ይህን ልምድ ሊወስዱ ይገባል ሲሉ የጉባኤው ተሳታፊወች ተናግረዋል፡፡
26ኛው አመታዊ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጅ የሽግግር ጉባኤ በዩኒቨርሲቲው መምህራ የተከናወኑ የሳይንስና ቴክኖሎጅ ሽግግርን የሚያመላክቱ የማህበረሰብ አገልግሎትና የምርምር ስራዎች በፕሮጀክት አቅራቢወችና በፈጠራ ባለቤቶች የቀረቡ ሲሆን ከጎንደር፣ ከአዘዞ፣ ከደሴ እና ከደብረታቦር መሰናዶና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጡ ተማሪዎች የምርምርና የፈጠራ ስራዎቻቸውን በኤግዚቢሽኑ አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም የዘንድሮው አመታዊ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የክኖሎጅ የሽግግር ጉባኤ ዩኒቨርሲቲው በትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኑን ያሳየና ዩኒቨርሲቲዉ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በሰፊው ያመላከተ ከመሆኑም በተጨማሪ ጉባኤው ከመስተንግዶው ጀምሮ ስኬታማ እንደነበር የጉባኤው ተሳታፊወች ገልፀው ዩኒቨርሲቲው ለወደፊት ለሚያደርጋቸው የምርምርና የማህበረሰብ አገልገሎት ስራዎች ተግባራዊነት ከዩኒቨርሲቲው ጎን መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ መሰረት አለምነህ
አርታኢ፡ ደምሴ ደስታ



