6ተኛው ሀገር አቀፍ የግእዝ ቋንቋ ጉባኤ ቅኔና ግብረ-ገብነት በሚል መሪ ቃል ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከኤፊድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ከብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ ጋር በጋራ በመተባበር 6ተኛውን ሀገር አቀፍ የግእዝ ቋንቋ ጉባኤ ግእዝና ግብረ-ገብነት በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 9-11ዓ/ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አልሙኒዬም ህንፃ አካሂዷል፡፡
በጉባኤው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ የኤፌድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ብዙነሽ መሰረት፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ኃላፊዎች፣ ከብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ፣የዩኒቨርሲቲ የቋንቋ እና ሥነ-ጽሑፍ እንዲሁም የግእዝ መምህራን፣የሀይማኖት አባቶችና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ከተለያዩ ተቋማት ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን በፕሮግራሙ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው የግእዝ ቋንቋ 3000 ዘመን ያስቆጠረ ከመሆኑም በላይ በዘመነ አክሱም ብሄራዊ ቋንቋ እንደነበርና ኢትዮጵያን በአለም አቀፍ የስነ-ጽሑፍ ጎራ ያስተዋወቀ ቋንቋ እንደሆነ አውስተዋል፡፡ የግዝ ቋንቋ በኢትዮጵያ ቀዳሚ የሆነ የሥነ-ጽሑፍ ቋንቋ በመሆኑ ያልዳሰሰው የእውቀት ዘርፍ እንደሌለና የህዝብ ታሪክ፣ የነገስታት ዜና መዋዕሎች፣ የፍልስፍና፣ የስነ-ከዋከብት፣ ህክምና መጻሕፍትና ሌሎች ተዘግበውበት የሚገኝ መሆኑን ዶ/ር አስራት አያይዘው ተናግረዋል‹‹
የግእዝን ቋንቋ ሀገራዊ ጥቅም የተረዳው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሚሰጣቸው የተለያዩ ከሀገር ውስጥና ውጭ ቋንቋዎች መካከል ከ2003ዓ/ም ጀምሮ በአጫጭር ጊዜ ስልጠና የተጀመረው ከ2011ዓ/ም ጀምሮ ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ እየሰጠ እንደሚገኝ ወደፊትም የሀገራችንን ሚስጥር፣ እውቀት፣ ጥበብና ታሪክ ለያዘው የግእዝ ቋንቋ እድገት ከሚሰሩ አካላት ጋር ሁሉ በመስራት ከጊዜው ጋር የተጣጣመ ስርአተ-ትምርት እንዲቀረፅ፣ በግእዝ የተፃፉ ጽሁፎች እንዲተዋወቁና ጥቅማቸው እንዲታወቅ የበኩላቸውን ተቋማዊ ግዴታ እንደሚወጡ ያላቸውን ቁርጠኝነት ዶ/ር አስራት አክለው ገልፀዋል፡፡
የኤፊድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ብዙነሽ መሰረት በጉባኤው የመክፈቻ ንግግራቸው በዚህ ጉባኤና አውደርዕይ ባለድርሻ አካላት ቋንቋው ላይ ጥናትና ምርምር ለማድረግ፣ በመዋቅር በአደረጃጀትና በስትራቴጅ የሚመራበትን አቅጣጫ ለማመላከት፣ በቋንቋው የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የመረጃ ሀብቶችን ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት ያላቸው ፋየዳ ለማስገንዘብና በዘርፉ የተሰሩ ጥናትና ምርምር ስራዎችን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል፡፡ ወ/ሮ ብዙነሽ አያይዘው በቋንቋው አማካኝነት የተከማቹ በርካታ እውቀቶችን አውጥቶ ለዘመናዊው የኑሮ ስርአት ጥቅም ላይ ለማዋልም ይሁን ለቋንቋዎች እድገትና ልማት አስተዋፅኦ እንዲያደርግ በሚመለከታቸው የመንግስት እና የባለድርሻ አካላት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥበት ቋንቋው እንዳይጠፋም መስራት እንደሚገባ አፅንዖት ሰጠው መልከታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመቀጠልም በተመረጡ የግእዝ መዛግብት የስነ-ምግባር አስተምህሮ እንደማሳያ፣የግእዝ ቅኔ ለግብረ-ገብነትና ሥነ-ምግባር ግንባታ ያለው አስተዋፅኦ፣ የግእዝ ሀብት ግብረገብነት ለሀገረ መንግስት ስርአት ግንባታ ያለው ሚና በግእዝ ቅኔ ማሳያነት፣ የግእዝ ሥነ-ጽሑፍ ሀብት ለግብረገብነትና ፍልስፍና ያለው ፋይዳ ከሀተታ ዘዘርዓ ያዕቆብ እና ከአንጋረ ምሰሌ ግእዝ መጻሕፍት አንፃር እና ሌሎች ጥናታዊ ጽሑፎች በአባ በአማን ግሩም፣ በዶ/ር ሙሉቀን አንዷለም፣ በመምህር ላእከማሪያም ብርሀኑ፣ በመ/ር አዲሴ አያሌው እና በሌሎች በዘርፉ ምሁራን ቀርቧል፡፡ የቀረቡትን ጥናታዊ ጽሑፎች መነሻ በማረግ ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡


ጉባኤውን አስመልክቶ በቅኔ መምህራን ቅኔ ቀርቦ፣ከብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ በተዘጋጀው አውደ ርእይ ጉብኝት ተካሂዶና ማጠቃለያ ውይይት ተደርጎ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡




