የፍሌም /FLAME/ (Faith Leaders Advocating for Maternal Empowerment)ፕሮጀክት በስድስት ጤና ጣቢያዎች ላይ በእናቶች ጤና ዙሪያ ያመጣውን ለውጥ ለባለድርሻ አካላት የማሳወቅ እና እውቅና የመስጠት ፕሮግራም አካሄደ
የፍሌም ፕሮጀክት ስኮፕ ከተባለው የዩኒቨርሲቲያችን አጋር ድርጅት፣ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ላለፉት አመታት ከቀድሞው ሰሜን ጎንደር ዞንና ከቀድሞው ሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ጋር በመተባበር ላለፉት ዓመታት በእናቶች እና በህፃናት ጤና ዙሪያ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

በመሆኑም ፕሮግራሙ ላለፉት ሁለት አመት ተኩል ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ከሆነባቸው ከቀድሞው ሰሜን ጎንደር ዞን ስር በሚገኙ በአባውራም፣ በሙሴባምብ፣ በአፀደ ማሪያም፣ በአምቦበር፣ በሳንጃ እና በጮንጮቅ ጤና ጣቢያዎች ያመጡትን ለውጥ ከሌሎች ከ12 ጤና ጣቢያዎች ጋር በማነፃፀር ፕሮጀክቱ ያደረገውን አስተዋዕፆ ለባለድርሻ አካላት ማሳወቅ እና ለተሳታፊዎችም ምስጋናና እውቅና መስጠትን አላማ ያደረገ እንደሆነ መ/ር ስመኘው ህንዴቦ ገልፀዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ጌታሁን አስረስ የጥናቱን ውጤት መረጃዎችን በመተንተን የተሰሩ ስራዎች፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች አስመልክቶ መጋቢት 3/2012ዓ/ም በማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት አዳራሽ አቅርበዋል፡፡

ዶ/ር ጌታሁን አያይዘው ፕሮጀክቱ ያስመዘገባቸውን ዋና ዋና ውጤቶች ማለትም፣ በጤና ጣቢያ የመጀመሪያ ክትትል የሚያደርጉ እናቶች ቅድመ ወሊድ ክትትል አንድ በ14 %፣ ቅድመ ወሊድ ክትትል አራትን በ26%፣ በጤና ጣቢያ የወሊድ አገልግሎት የማግኘት መጠን በ11 % ማሻሻል እንደተቻለ በዝርዝር ለባለድርሻ አካላት አቅርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

በመጨረሻም ከፕሮጀክቱ ጋር ሲሰሩ ለቆዩ የሀይማኖት አባቶች፣ በልማት ቡድን የተደራጁ እናቶች እና የጤና ጣቢያ ሀላፊዎች እውቅና ተሰጥቶ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡



