ስምንተኛው የባንዲራ ቀን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥቅምት 8/2008 ዓ.ም ስምንተኛን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ባከበረበት ወቅት የሀገራችን እድገት ለማስቀጠል አባቶቻችን መስዋዕትነት የከፈሉባትን ይህ ትውልድም በልማት ከፍ ያደረጋትን ባንዲራችን መገለጫችን በመሆንዋ ዩኒቨርስቲያችን ዕለቱን በድምቀት ያከብራል ሲሉ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ ገልጸዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ “በህዝባዊ ተሳትፎ ህዳሴዋን ለማረጋገጥ ሰንደቅ ዓላማውን ከፍ ከፍ በማድረግ እየተጋች ያለች አገር- ኢትዮጵያ!” በሚል መሪ ቃል የተከበረው ስምንተኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ግቢ በድምቀት ተከብሯል ።

ስምንተኛውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ስናከብር በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን መርሀ ግብር የተያዙ ግቦችን በተሟላ ሁኔታ በመፈጸም የህዳሴ ጉዞ ለማሳለጥ ዳግም ቃል የምናድስበት እንደሚሆን ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ገልጸዋል።
ቀደምት አባቶቻችን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለውን ሰንደቅ ዓላማችን በማውለብለብ በየዘመናቱ የመጡ የውጭ ወራሪ ሃይሎችን ለመደምሰስ በቅተዋል ያሉት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ የብሄራዊ ኩራትና የሉዓላዊነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ አላማ ታሪክ፣ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ አበክረው አስረድተዋል ።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ማክበራችን ሁላችንም በየተሰማራንበት የስራ ዘርፍ የጽናት መንፈስን በመሰነቅ ዓላማችንን ከግብ የምናደርስበት ዋና ተምሳሌታችን ሊሆን ይገባል የሁሉም የበዓሉ ታዳሚዎች ስሜት ነበር፡፡
የባንዴራ መስቀል መርሃ ግብር ሲፈፀም የዩኒቨርሲቲው ከፈተኛ አመራሮች በቦታው የተገኙ ሲሆን በራካታ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች የፕሮግራሙ ታዳሚዎች ነበሩ፡፡

