የአካል ጉዳተኛ ሰራተኞች ማህበር ተቋቋመ

የአካል ጉዳተኛ ሰራተኛች ማህበር ሲመሰረት
“የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካል ጉዳተኛ ሰራተኞች ማህበር” ጥቅምት 30/2008 ዓ.ም በማኔጅመንት አዳራሽ በይፋ ተመሰረተ፡፡ በዕለቱ የተለያዩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካል ጉዳተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች፤ CBR ፕሮግራም፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካል ጉዳት ምርምርና አገልግሎት መስጫ ማእከል እና ሌሎችም አጋር ድርጅቶች የተገኙ ሲሆን የማህበሩ ደንብና መመሪያ በማህበሩ ፕሬዚዳንት በአቶ ምስጋናዉ ሰማኝ አማካኝነት ቀርቦ ሰፊ ዉይይት ከተካደ በኋላ የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ ተካሂዷል፡፡
ማህበሩ አካል ጉዳተኛ የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ አባላትን መብትና ጥቅም ለማስከበር፣ በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎችን ለመስራት፣ ሌሎች የአካል ጉዳኞች ማህበራትን ለማጠናከር እና በተለያዩ የህይወት ክህሎት እና መሰል ስልጠናዎች የአካል ጉዳተኛ ሰራተኞችን አቅም ማጎልበት ዓላማ አድርጎ የተመሰረተ መሆኑ ተገለጧል፡፡
ማህበሩ በቀጣይ አካል ጉዳትን ከመከላከልና በሁሉም መስክ አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ እንቅስቃሴ እንዲኖር፣ አካል ጉዳተኛ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር በርካታ የግንዛቤ ማሳደጊያ ስራዎችን ለመስራት ማቀዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

አቶ አሸናፊ የCVR ፕሮግራም አሰተባባሪ ስለ ማህበሩ አመሰራረት ንግግር ሲያደርጉ
በመጨረሻም አካል ጉዳት መቸ እና እንዴት ሊከሰት እንደሚችል የሚታወቅ ባለመሆኑ ሁሉም የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ አባላትና ከፍተኛ አመራሩ ለማህበሩ መጠናከር በገንዘብ በሃሳብ እና በቁሳቁስ እርዳታ በማድረግ የበኩላቸዉን አስተዋፆ እንዲያበረክቱ፣ በተጨማሪም ተባባሪ እና የክብር አባል በመሆንም ለማህበሩ እና ለአካል ጉዳተኞች ያላቸዉን አጋርነት በማሳየት ወደፊት የሚጠበቅባቸው መሆኑ ተገልጧል፡፡

