የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለዶ/ር መርሻ ጫኔ የሙሉ ፕሮፌሰርሽፕ ማዕረግ ሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ህዳር 2008 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ህክምና ፋካልቲ በመምህርነት እያገለገሉ ላሉት ወጣት ተመራማሪ ለዶ/ር መርሻ ጫኔ የሙሉ ፕሮፌሰርሽፕ የአካዳሚክ ማዕረግ ሰጠ፡፡ፕ/ር መርሻ ጫኔ በምስራቅ ጎጃም ዞን በእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ በደብረፅዮን ቀበሌ በ1972 ዓ.ም መስከረም 01 ቀን ተወለዱ፡፡ አባታቸዉ አቶ ጫኔ ከበደ ሲሆኑ እናታቸዉ ደግሞ ወ/ሮ አንችነሽ በየነ ይባላሉ፡፡

ፕ/ር መርሻ ጫኔ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአካባቢያቸዉ ባለመኖሩ ወደ ቄስ ትምህርት ቤት ገብተዉ ለአንድ ዓመት ያህል ፊደል ከቆጠሩ በኋላ በቀጣዩ ዓመትም በአካባዉ በሚገኝ የመሰረተ ትምህርት መስጫ ጣቢያ ገብተዉ ተምረዋል፡፡ ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ የእግር መንገድ መጓዝ እንደሚችሉ ሲረጋገጥ ድቦ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ከመኖሪያ ቀበሌያቸዉ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዉ በመርጦ ለማርያም ወረዳ ዋና ከተማ የአብርሃ አፅብሃ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመግባት ከ9-12ኛ ክፍል ትምህርታቸዉን ተከታትለው በ1991 ዓ.ም ያጠናቀቁ ሲሆን በአገኙት ከፍተኛ ዉጤት በ1992 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ በመግባት ትምህርታቸዉን በመማር የመጀመሪያ ዲግሪያቸዉን 1997 ዓ.ም በእንስሳት ህክምና የዶክትሬት ዲግሪ ለማግኘት ችለዋል፡፡ በወቅቱ የትምህርት ሚኒስቴር በውጤታቸው ለተሻሉ ተማሪዎች የትም/ት ዕድል ይሰጥ ስለነበር የመደበኛ ሠራተኝነት ቅጥር ፈፅመዉ በቀጥታ ከ1998-1999 ዓ.ም ባገኙት የትምህርት ዕድል የሁለተኛ ዲግሪያቸዉን ተምረዋል፡፡
ከዚያም ከሐምሌ 01.2003 ዓ.ም ጀምሮ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመድበዉ በተለያዩ ጊዜያት የዓመቱ ምርጥ ተመራማሪ፣ የዓመቱ ምርጥ መምህር በመባል ሽልማቶችን ከዩኒቨርሲቲዉ አግኝተዋል፡፡
ፕ/ር መርሻ ጫኔ ይህን የአካዳሚክ የመጨረሻ ማእረግ በዚህ የወጣትነት ዕድሜያቸዉ እንዲያገኙ የረዳቸዉን የምርምር ስራዎችን ስንመለከት ሁለት መፅሐፍትን ያሳተሙ ሲሆን 115 ያህል ጆርናሎችን በማዘጋት ለህትመት አብቅተዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ወጣቱ ፕ/ር መርሻ ጫኔ ባገኙት ከፍተኛዉ የአካዳሚክ ማዕረግ ደስታ የተሰማዉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ በራሳቸዉና በዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ ስም እንኳን ደስ ያለዎት ብለዋል፡፡

