የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ሪፈራል ሆስፒታል ስራ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ነው
ከአሜሪካ መንግስት በተገኘ 180 ሚሊዮን ብር (አንድ መቶ ሰማንያ ሚሊየን ብር) ድጋፍ የተገነባዉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታሉን ስራ ለማስጀመር የሰነድ መፈራረምና ቁልፍ እርክክብ ተካሂዷል፡፡ ሠነዱን የተፈራረሙት በኢትዮጵያ የCDC ማኔጅመንት አባል እና ተባባሪ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሥርጉት አየለ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አኒሳ በፈቃዱ ናቸዉ፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ሲጎበኝ፡፡
በስነ-ስርዓቱ ላይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ክቡር ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል፣ የሰሜን ጎንደር ዞና ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግዛት አብዮ፣ የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ጌትነት አማረ እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸዉ የክብር እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ የክብር እግዶቹ ወደ 400 የሚጠጉ የሪፈራል ሆስፒታሉን ክፍሎች ተዘዋውረው ከጎበኙ በኋላ ከእንግዳ ማረፊያ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ቀዶ ህክምና ክፍል እና የመዝናኛ ክፍል ድረስ በየህክምና ዘርፉ በጥራት ተገንብቶ ለርክክብ እንደቀረበ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በቀጣይ ሆስፒታሉ የሚጠበቅበትን አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር በኢትዮጵያ የ ሲዲሲ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሀንሰን ጄፍ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ቁልፍ አስረክበዋል፡፡

ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ከወ/ሮ ሥርጉት አየለ እና ከዶ/ር አኒሳ በፈቃዱ ስነድ ሲፈራረሙ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ክቡር ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ኢትዮጵያ በጤናዉ ዘርፍ እያበረከተችዉ ያለዉ አስተዋጽኦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸው ለታየው ለውጥ መምጣት ሀገራችን መከላከልን መሠረት ያደረገ የጤና ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረጓ እና ከሌሎች ረጅ ሃገራት ጋር የዲፕሎማሲ ስራ መስራት በመቻሏ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ ህዝብ ያደረገዉን ድጋፍ በህዝባችን ስም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

ክቡር ዶ/ር ስንታየው ወ/ሚካኤል ሪፈራል ሆስፒታሉን አስመልክተው ንግግር ሲያደርጉ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲያችን ከአሜሪካ መንግስት ጋር የ60 ዓመት የአብሮነት ጉዞ ያለው መሆኑን ገልፀው ከሙያዊ ድጋፍ እስከ ማቴሪያል ልገሳ ድረስ ለሆስፒታሉ ሲያበረክት የቆየ ሲሆን በአሜሪካን መንግስት ትብብር የተገነባዉ ሪፈራል ሆስፒታሉ የህብረተሰቡን የጤና ችግር የሚፈታ እንደሆነም ለተደረገው ድጋፍ በዩኒቨርሲቲዉና በራሳቸዉ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የCDC ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሃንሰን ጄፍ በበኩላቸዉ ሪፈራል ሆስፒታሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ እንዳስደሰታቸዉ እና በቀጣይም ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር ያላቸዉን ግንኙነት አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል፡፡ አያይዘዉም ሪፈራል ሆስፒታሉን ለማጠናከር የቁሳቁስና ሌሎችንም ድጋፎች ለማደረግ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡

ዶ/ር ደሻለኝ መንገሻ ከዶ/ር ሃንሰን ጄፍ ቁልፍ ሲረከቡ፡፡
//ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት//

