በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስለስደት ግንዛቤ ማስጨበጫና ስራ ፈጣሪነት በዳባት ወረዳ ለሚገኙ 60 የገጠር ወጣቶች ከሚያዝያ 18-20/2008 ዓ.ም ስልጠና ተሰጠ

የአንዲትን ሀገር የእድገት እጣ ፋንታ ከሚዎስኑት ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ህዝብ ነው፡፡ በእርግጥ ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ቁጥር ለአንዳንድ ታዳጊ ሀገራት ለድህነታቸው ዋነኛ ምክንያት ሊሆን ቢችልም ለሌሎች እንደቻይና ላሉ ሀገራት ደግሞ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ያደርጋል፡፡
ከዚህ እሳቤ በመነሳት በማህበረሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉትን ችግሮች በመለየት ፣ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በማጥናትና መፍትሄ በመስጠት የሚታወቀው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በዳባት ወረዳ ለሚገኙ ስልሳ የገጠር ወጣቶች ከሚያዝያ 18-20/2008 ዓ.ም ስለስደት ግንዛቤ ማስጨበጫና ስራ ፈጣሪነት ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የስልጠናውን አስፈላጊነት አስመልክተው የዳባት ወረዳ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች አስተባባሪ አቶ ዳንኤል ታረቀኝ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ስልጠናው የአካባቢውን ብሎም የሃገሪቱን አሳሳቢ ጉዳይ በመለየት አምራች ለሆነው ወጣት ክፍል ጥሩ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ በመሆኑ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ያሉ ሲሆን በመቀጠልም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ኮሌጅ ማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ፈንታው የስልጠናውን አላማ አስመልክተው እንደገለጹት ለሶስት ቀናት የሚሰጠው ስልጠና የገጠር አካባቢ ወጣቶች ስለስደት ያላቸው ግንዛቤ እንዲሰፋና የስራ ፈጣሪነት ተነሳሽነታቸው እንዲጨምር በማድረግ ይህ አምራች የሆነ የህብረተሰብ ክፍል ከስደት ህልም ወጥቶ ባደገባት ቀየና ሀገር በመስራት ራሱንና ወገኑን ብሎም ሃገሩን በመርዳት ክብሩንና ህይዎቱን ጠብቆ እንዲኖር ለማስቻል ነው፡፡
ስልጠናውን በትብብር አዘጋጅተው የሰጡት አምስት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ኮሌጅ መምህራን ሀይማኖት አትንኩት፣ ሀይማኖት ጓዴ፣ንጉሴ አህመዲን በየነ ደርሶ እና ገናነው አየነው ሲሆኑ በተለይ ስደትን አስመልክተው ወጣቱ ክፍል ትርፍ ሀገርና ህይዎት ያለው ይመስል ክብሩንና ምትክበ የሌላት ህይዎቱን ለአረመኔዎች አሳልፎ የሚሰጥበት ጊዜ አሁን ሊቆም ይገባዋል፤ስደትን እያሰበ የሚኖር ወጣት ስራ ሊፈጥር አይችልምና በቅድሚያ የስደት ሀሳብ ከወጣቱ ህሊና ሊወጣ ይገባዋል፤በሃገር ስንሰራ የሚያኮራትርፍ ባናገኝ እንኳን ከህይዎትና ከክብር ኪሳራ ነጻ ነን በማለት ለተሳታፊዎች የገለጹ ሲሆን እንዲሁም አሁን በአለማችን የቢሊየነር ምሳሌ የሆኑት ባለሃብቶች በመንግስት ስራ ወይም በስደት ሳይሆን በብርቱ የስራ ፈጣሪነታቸው ነውና ወጣቶች በትንንሽ መሰናክሎች ቶሎ ተስፋ ሳይቆርጡ ራሳቸውን ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ፈታኝ ነገሮች ቅድሚያ ተዘጋጅተው በመጠበቅ ጠንክረው ከሰሩ ራሳቸውንና ሀገራቸውን የማይለውጡበት ምክንያት እንደሌለ ለሰልጣኝ ወጣቶች አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ደስታው ዋኘው

