ለተመራቂ አከል ጉዳተኛ ተማሪዎች ሽልማት ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካል ጉዳት ጥናት እና አገልግሎት መስጫ ማእከል ከECDD ጋር በመተባበር በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ 5ወንድና 2 ሴት በድምሩ ለ7 ተመራቂ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ሰኔ 7/2008 ዓ.ም የአልባሳት ሽልማት ሰጠ፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካል ጉዳት ጥናት እና አገልግሎት መስጫ ማእከል አስተባባሪ ወ/ሮ ህይወት አበበ እንደገለጹት ሽልማቱ ከ1ኛ እስከ 4ተኛ ለወጡ ወንድ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሸሚዝና የጅንስ ሱሪ እንዲሁም ከ5ተኛ እስከ 7ተኛ ለወጡ የሸሚዝ ስጦታ እንደሆነና በተመሳሳይ ለሁለቱ ሴት አካል ጉዳተኛ ተመራቂ ተማሪዎች የብር አንገት ሐብልና የቦርሳ ሽልማት እንደተደረገላቸው ገልፀዋል፡፡ አስተባባሪዋ ወ/ሮ ህይወት አያይዘውም ይህ ሽልማት የተደረገበት ምክንያት ተማሪወቹ ይህን የማድረግ አቅም ስለማይኖራቸው ለስራ ፍለጋ ወደተለያዩ ቦታወች በሚንቀሳቀሱበት እና ለቃለመጠይቅ በሚቀርቡበት ወቅት ራሳቸውን ጠብቀው መቅረብ እንደሚያስችላቸው ታስቦ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የሽልማት ስርአቱን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሆነ ማንደፍሮ የአካል ጉዳተኝነት በማንኛውም ሰአት በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል መሆኑን እና የአካል ጉዳተኛ ማለትም አለመቻል አለመሆኑን አስታውሰው ይህን አስተሳሰብ በማሰተማርና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት እየሰራ ያለው የጎንደር ኒቨርሲቲ የአካል ጉዳት ጥናት እና አገልግሎት መስጫ ማእከልተስፋ ሰጭ የሆኑ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ሽልማቱም ለተማሪወቹ እውቅና የመስጠትና ተማሪወቹ ከተመርቁ በኃላ በስራ ምክንያት ማህበረሰቡን በሚቀላቀሉበት ወቅት በተለይ በገጠሩ አካባቢ እስከ አሁን ድረስ በኣካል ጉዳተኝነታቸው ምክንያት ቤት ተቆልፎባቸው የሚገኙ ህፃናትን ካሉበት በማውጣትና እነሱ ያገኙትን ዕድል እንዲያገኙ ብሎም በማህበረሰቡ ያሉ ችግሮችን በመፈለግ በጥናትና ምርምር ለመፍታት የሚችሉ ጉዳዮችን ለዩነቨርሲቲው በማድረስና በማመላከት በኩል የራሳቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ ለመሳሰብ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የሽልማቱ ተሳታፊ የሆኑ ተመራቂ የአካል ጉዳተኛ ተማሪወች በተደረገላቸው ሽልማት የዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳት ጥናት እና አገልግሎት መስጫ ማእከሉንና ECDD የተባለውን አጋር ድርጅት በማመስገንና የተለያዩ ግጥሞችን፣ወጎችንና ዜማወችን በማቅረብ ዝግግቱን አጠናቅቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ መሰረት አለምነህ
አርታኢ፡ ደምሴ ደስታ

