የቴክኖሎጂ ኢንስቲዩት የኪነ- ህንጻ እና የሲቪል ምህንድስና ተማሪዎችን በደማቅ ሁኔታ አስመረቀ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 5 ዓመት ከመንፈቅ የመደበኛ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወንድ 33፣ ሴት 16 በድምሩ 49 የኪነ-ህንጻ እጩ ተመራቂዎችን በኢንስቲትዩቱ ግቢ አስመርቋል፡፡ በተመሳሳይ በተከታታይ መርሀ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ የሲቪል ምህንድስና ተማሪዎች ወንድ 18፣ ሴት 2 በድምሩ 20 ትምህርታቸውን አጠናቀው የካቲት 3/2010 ዓ.ም ከኪነ-ህንጻ ተማሪዎች ጋር በደማቅ ሁኔታ ለምረቃ አብቅቷል፡፡
በአነስተኛ ህንጻዎችና የሰው ኃይል ስራ የጀመረው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአሁኑ ሰዓት በርካታ መሰረተ ልማቶችና የማስፋፊያ ስራዎች የተሰሩለትና አሁንም በመሰራት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት የጎንደር ዩኒቨርሰቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ናቸው፡፡ ዶ/ር ደሳለኝ በመሰረተ ልማት በኩል፣ 10 ህንጻዎችን አንድ ላይ ያስተሳሰረ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የምህንድስና ወርክሾፕና የምርምር ማዕከል፣ የላቭራቶሪ እቃዎች በከፊል እየተሟሉለታና አሁን በመጣናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ለአብነት አንስተዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ሙያተኞች ማህበረሰቡን ለማገልገል በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆናቸውን ለመጠቆምም ሙህራኑ ጣናን እያጠቃ ያለውን የእንቦጭ አረም ማስወገጃ ተንሳፋፊ የሞተር ጀልባ የሰሩ መሆናቸውን ገልጸው በአሁኑ ስዓት በሙከራና በማሻሻያ ስራ እንደሚገኝ ዶ/ር ደሳለኝ በንግግራቸው አንስተዋል፡፡
[widgetkit id=8314]
ፕሬዝዳንቱ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ “በዩኒቨርሰቲው በነበራችሁ ቆይታ ለህይወታችሁ የተግባር መነሻ የሚሆናችሁ እውቀትና ክህሎት ቀስማችኋል፤ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ጊዚያዊ ችግሮች ሳይፈትኗቸሁ ዛሬ ለመጀመሪያው የስኬት ምዕራፍ ደርሳችኋል፤ በመሆኑም ባገኛችሁት እውቀትና ክህሎት ተጠቅማችሁ ለዚህ ላበቃችሁ ህዝብ ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ ለማበርከት ፍፁም የተግባር ሰው መሆን ይጠበቅባችኋል፡፡ የመማር ውጤት የሚለካው በሀገር ዕድገትና በህዝብ ኑሮ ላይ በሚመዘገብ ለውጥ ነው፡፡ ለዚህ ተግባራዊነት ደግሞ እናንተ ብሉሹ አሰራርንና ኢ-ስነምግባራዊ ድርጊቶችን መዋጋት ይጠበቅባችኋል፡፡” በመጨረሻም ቃል ኪዳን አክባሪ፣ ለሀገር ተቆርቋሪ፣ የልማትና የእድገት አርበኛ እንዲሆኑ የአደራ መልዕክታቸውን ዶ/ር ደሳለኝ አስተላልፈዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ም/ፐሬዚዳንቶች፣ የክብር እንግዶች፣ የኢንስቲቲዩቱ መምህራን እንዲሁም የተመራቂ ተማሪዎች ወላጆች በተገኙበት፣ በሚገባ ትምህርታቸውን ላጠናቀቁ የኪነ-ህንጻና የሲቭል ምህንድስና ዕጩ ተመራቂዎች፣ እንኳን ለዚህ ቀን አደረሳችሁ በማለት መመረቃቸውን ያበሰሩትና የምረቃ ስነስርዓቱን ያስፈጸሙት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ብርሀኑ ሙላት ናቸው ፡፡
በትምህርት ቆይታቸው ባጠቃላይ ውጤት አብልጫ ነጥብ ላስመዘገቡ ወንድና ሴት ተመራቂዎች፣ በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት ዓፀደወይን አስፋጻሚነት በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከኪነ-ህንጻ ት/ት ክፍል ከወንዶች አርክቴክት ናትናኤል ንጋቱ 3.72 በማምጣት ተሸላሚ ሲሆን ከሴቶች አርክቴክት ሰራዊት አያልቅበት 3.52 በማምጣት ተሸላሚ ሆናለች፡፡ ከሲቪል ምህንድስና ት/ት ክፍል ከወንዶች ኢንጂነር ስንታየሁ ዳሰው 3.79 በማምጣት ተሸላሚ ሲሆን ከሴቶች ደግሞ ኢንጅነር አቦነሽ ግርማ 3.2 በማምጣት ተሸልማለች፡፡
ዘጋቢ፡- አምሳሉ ግዛቸው
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

