የጉና ተራራን በመጠበቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው
የበርካታ ብዝሀ ሕይዎት መገኛ የ41 ወንዞች፣ የ77 ምንጮች መነሻ የሆነው የጉና ተራራ በአሁኑ ሰዓት 4615 ሄክታር ስፋት አለው፡፡ በውስጡ 96 ያህል የእፅዋት ዝርያዎች፣ 139 የአዕዋፍ ዝርያዎች 30 ያህል አጥቢ እንስሳት አንዲሁም በመጥፋት ላይ የሚገኙት የቀይ ቀበሮ እና የጭላዳ ዝንጀሮዎች እንደሚገኙ የጉና ተራራ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ፅ/ቤት ባለሙያዎች ከሰጡተ ገለፃ እና ካዘጋጁትበራሪ ወረቀት መረዳት ችለናል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የቱሪዝም ትምህርት ክፍል ለመከለልና ለመጠበቅ እንዲሁም ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ በመመለስ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠት እና የጉና ተራራ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ፅ/ቤት እንዲቋቋም የራሱን አስተዋፅኦ ሲያደርግ መቆየቱን አቶ አሉበል ወርቂ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቱሪዝም ትምህርት ክፍል ኃላፊና የጉና ተራራ ፕሮጀክት አስተባባሪ ገልፀዋል፡፡ ፅ/ቤቱ ከተቋቋመ በኋላም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ መጋቢት 14 እና 15 2010 ዓ.ም ከጉና ተራራ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ፅ/ቤት ጋር በመተባበር ለጉና አካባቢ ተወላጆች፣ ለሀይማኖት አባቶች፣ ለሴክተር መስሪያ ቤት ሀላፊዎችና ለባለሙያዎች በደብረታቦር ከተማ የግንዛቤ ፈጠራ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡
[widgetkit id=8794]
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የጉና ተራራ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ጽ/ቤት ኃላፊ መቶ አለቃ ፈንቴ መብራቱ የጉና ተራራን በመጠበቅ ሀገራችን ለያዘችው የልማት ጉዞ ለማፋጠን የበርካታ ወንዞች ምንጭ የሆነውን ይህን ስፍራ በአካባቢው ህብረተሰብ አስጠብቆና ተንከባክቦ ለቀጣይ ትውልድ መሰረት ለመጣል፣ በዙሪያው የሚገኙ ታሪካዊ ገዳማት እንዲሁም ፍል ውኃዎችና ሌሎችንም መስህቦች የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሚገኝና ለዚህም ስፍራው ከተጠበቀ በኋላ በርካታ ለውጦች መታየታቸውን ገልፀው የጎንደርን ዩኒቨርሲቲ ላደረገው ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በዚህ ስልጠናም ብዝህ ህይዎት ምንድን ነው? በጉና ተራራ ምን አይነት ብዝሀ ህይዎት ይገኛሉ? ለምንስ ያገለግላሉ ባለቤታቸው ማን ነው? ወደፊትስ እጣ ፈንታቸው ምንድን ነው? በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ተሳታዎች የተወያዩበት አንዱ ሲሆን የጉና ተራራ ስነ ምህዳር እና አሁን ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ስፍራው ከተጠበቀ በኋላ ስፍራውን ወደ ስራ ቀይሮና አዳዲስ ሰራ ፈጥሮ ህብረተሰቡን እንዴት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል? በሚል በስራ ፈጠራ እና አደጋ ቢከሰት እንዴት መከላከል ይቻላል በሚል በአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ዙሪያ ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡ ስልጠናው በውይይት የዳበረ ሲሆን፣ የጉና ተራራ ጥብቅ ስፍራ በዘላቂነት ተጠብቆ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ያሉ ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው ላይም ውይይት ተደርጓል፡፡
የጉና ተራራ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ፣ ለትምህርትና ለምርምር ስራ፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ መዝናኛ እንዲሆን እና ከዚህም ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደሚያስፈልግ ተወያዮች ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ወጣቱ ከግብርና ውጭ ባሉ የስራ መስኮች ቢሰማራ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ በመፍጠር እና የተሸሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በማጥናት ዩኒቨርሲቲዎች የማሀበረሰቡን አመለካከት የመቀየር ስራ በመስራት ከጎናቸው እንዲሆን ተወያዮች አንስተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎችም ከተቋቋሙበት ዋንኛ ተልዕኮዎቻቸው መካከል ማህበረሰቡን ማገልገል አንዱ ተግባር ነውና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ ያለው መልካም ተግባር ይበል ያሰኛል፡፡ የተጀመረውን መልካም ተግባር ጫፍ ደርሶ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ተረጋግጦ እና የጉና ተራራ ወደ ቀድሞ እይታው ይመለስ ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡
ዘጋቢ፡ መሰረት አለምነህ
ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

