አዲስ የካሪኩለም ግምገማ ተደረገ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርማቲክስ ፋካሊቲ ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ት/ት ክፍል፣ ኢንፎርሜሽን ሳይንስ ማስተርስ ዲግሪ በዳታ ሳይንስ(masters of information science degree in data science) በሚል የትምህርት ዘርፍ በሚቀጥለው ዓመት(በ2011 ዓ.ም) ለመጀመር የሚያስችለውን የካሪኩለም ግምገማ በዘርፉ ሙህራን ሚያዚያ 12/2010 ዓ.ም በአጼ ቴዎድሮስ ግቢ የድህረ ምረቃ አዳራሽ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት ዓጸደወይን በተገኙበት አድርጓል፡፡
በውይይቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርማቲክስ ተማሪዎችና መምህራን የተገኙ ሲሆን ከብሄራዊ የመረጃ መረብ ደህንነት ተቋም/INSA/፣ ከጀርመን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት/GIZ/ እንዲሁም ከመቀሌና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡ የዘርፉ ሙህራንም ተሳትፈዋል፡፡
[widgetkit id=8983]
የዳታ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ በማስተርስ ዲግሪ ደረጃ በሀገሪቱ እስካሁን እንደማይሰጥ የገለጹት የኢንፎርሜሽን ሳይንስ ት/ት ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ አሰፋ ቸኮል የት/ት ክፍሉ በዳታ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ በሚቀጥለው ዓመት ማለትም በ2011 ዓ.ም በማስተርስ ድግሪ ደረጃ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር እንዲቻል ለማድረግ የካሪኩለሙ ግምገማ ዋና ዓለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመጪው ዓመት ወደ ስራ ይገባበታል የተባለው የዳታ ሳይንስ ካሪኩለም አጠቃላይ ሁኔታ ምን እንደሚመስል በገለጻ የአብራሩት የኢንፎርሜሽን ሳይንስ መምህርና የዩኒቨርሲቲው የቤተመጻህፍትና ዶክመንቴሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለህኝ አዳነ ናቸው፡፡ በመቀጠል ከአዲስ አበባ የመጡት ዶ/ር ጥበበ በሻና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶ/ር አቢዮት ሲናሞ በካሪኩለሙ ላይ ያላቸውን ሙህራዊ ግምገማ በገለጻ አስረድተዋል፡፡
ተሳታፊዎች የቀረቡትን ጽሁፎችና ገላጻዎች መሰረት በማድረግ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፤ ለወደፊትም ይበጃል ያሏቸውን ሀሳቦች በመለገስ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
ዘገባ፡ አምሳሉ ግዛቸው
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

