የዓለም የዓሣ ስደት ቀን በዓል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አሰተባባሪነት ተከበረ
የዓለም የዓሣ ስደት ቀን በዓል መከበር ከጀመረ አንስቶ ኢትዮጵያም እስካሁን ድረስ እያከበረች ትገኛለች፡፡ በዓሉ በዓለምና በኢትዮጵያ ለ3ኛ ጊዜ እየተከበረ ሲሆን ሁለቱ በባህርዳር ከተማ ጣና ዙሪያ ላይ ’’የጣና ሃይቅ ዙሪያ አሣዎቻችን እንታደግ’’ በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት የሩጫና የጀልባ ውድድር በማካሄድ ሲከበር ቆይቷል፡፡
3ኛው የዓለም የዓሣ ስደት ቀን በጎንደር ዙሪያ ጣና ሃይቅ ላይ ’’የጣና ሃይቅ ዓሣዎችን ከእንቦጭ አረም ጥቃት እንታደግ’’ በሚል መሪቃል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ሚያዝያ 13/2010 ዓ.ም ተከብሯል፡፡ በዓሉ የተከበረበት ዋና ዓላማ የጣና ሃይቅ አሣዎች በእንቦጭ አረም ምክንያት ቀጣይ ህይዎታቸው ችግር ውስጥ በመሆኑ በርካታ የዓሣ ዝርያዎችን ለመታደግ ርብርብ እንዲደረግ ችግሩን ለኢትዮጵያና ለዓለም ሃገራት ለማሳሰብ እንደሆነ ተገጿል፡፡
[widgetkit id=9032]
በበዓሉ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣የጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ቢሮ ተዎካዮችና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ህትመት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘውዱ ተሾመ ጣና ሃይቅ በተከሰተው የእንቦጭ አረም ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ የማሀበረ-ሰብ እንቅስቃሴና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ምርምር ሲሰራ መቆየቱ የሚታወስ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን አመርቂ ውጤት መምጣት ባለመቻሉና ወደፊት በዓሣ ሀብቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ ለመግታት ዩኒቨርሲቲዎች በቅንጅት መስራታቸውን ለመግለፅ ታስቦ የተካሄደ ፕሮግራም መሆኑን ገልጸው በቀጣይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የሚሰራ መሆኑን በመልክታቸው አስተላልፈዋል፡፡
በዓሉን በተመለከተ ፕ/ር አበበ ጌታሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዞሎጂካል ትምህርት ክፈል ሃላፊና የዓለም የዓሣ ስደት ቀን አስተባባሪ ኮሚቴ አባል፣ ከ80 በላይ በተቀናጁ የዓለም ሃገራት በተለየዩ 50 መድረኮች ላይ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በጣና ሃይቅ ውስጥ ነጭ የዓሣ ዝርያዎች የሚገኙ ቢሆኑም በእንቦች አረም ጥቃት ምክንያት ወደፊት መራባት እንደማይችሉ የችግሩን አሳሳቢነት አክለው ገልጸዋል፡፡ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ጣና ሀይቅ ልዩ ቦታው አግድ ቅርኛ እና ምጥረሀቦ ዋርካ በሚባሉ ቦታዎች ከፍተኛ የዓሣ ምርት እየተመረተ፡፡
ወደ አዲስ አበባ ይላክ እንደነበርና በአሁኑ ሰዓት የዓሣ ምርቱ የተቋረጠ መሆኑን ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የጣና ሀያቅ ብዝሃ ህይዎት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አያሌው ወንዴ ገልጸዋል፡፡
ለዚህ አንገብጋቢ ችግር መፍትሄ ይሆናል ያሉት ደግሞ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በውሃና ዓሣ ሀብት ምርምር ላይ የሚታወቁት ዶ/ር ዋሴ አንተነህ የእንቦጭ አረም በዓሣዎችና በሥነ መህዳር ላይ የሚያደርሰውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተባበረ የሰው ሀይልንና የሃርቨስተር ማሽን መጠቀሙ እንዳለ ሆኖ ዋናው ግን ነፍሳትን በማራባትና ወደ ሃይቁ በመልቀቅ የሚደረገው የምርምር ሥራ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ልምድም በቪክቶሪያ ሃይቅና በግብፅ ሃይቆች ላይ ሥራ ላይ ውሎ ውጤታማ መሆኑን ጠቁመው ነፍሳትን ከ1 ዓመት በፊት ከኡጋንዳ ሃገር በማስመጣት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ሥራ እየተሰራ የሚገኝ መሆኑንና ሥራው 80% መድረሱን አያይዘው ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- በላይ መስፍን
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

