
“Online Journal System” የሚል ሶፍትዌር ለማስተዋዎቅ የሚያስችል አውደ ጥናት ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ የኤዲቶሪያል ክፍል አዘጋጅነት “On line journal system” የሚል ሶፍትዌር ማስተዋዎቅ የሚያስችል አውደጥናት ሰኔ 28/2013 ዓ.ም በሳይንስ አምባ ፒ ኤች ዲ አዳራሽ ተካሔደ።
በአውደ ጥናቱ የተለያዩ የሚመለከታቸው የኮሌጁ ማህበረሰብ አባላት፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ ዳይሬክተሮች እና መምህራን ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ጤና ሳይንስና ባዮ ሜዲካል ሳይንስ ጆርናል ከ13 አመት በፊት የተከፈተ ሲሆን ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ተከትሎ ተቋሙ የሰራው ተግባር ለአገር አቀፍና ለአለም አቀፍ የሳይንስ ማህበረሰብ ትውውቅ መደረጉን የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ አካዳሚክ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ በመክፈቻ ንግግራቸው ተናግረዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ህትመት አገልግሎት ስር ያሉ የተለያዩ የምርምር ውጤቶች ከሚታተሙባቸው ጆርናሎች መካከል አንዱ በህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የዚህ አውደጥናት አላማም በአሁኑ ሰዓት መፅሄቱን ለማዘመንና ለማቀላጠፍ ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ መረጃን የትኛውም ቦታ ሆኖ መለዋወጥ የሚያስችል ሶፍት ዌር ለማስተዋወቅ እንደሆነ ዋና አርታኢ ዶ/ር አስቻለው ገላው ተናግረዋል፡፡
በአውደጥናቱ እስከአሁን ያጋጠሙ ፈተናዎች እና መልካም አጋጣሚዎችን የተመለከተ ገለጻ በዶ/ር አስቻለው ገላው እንዲሁም ይህን አዲስ ሶፍትዌር ለመጠቀም የሚያስችል ማብራሪያ በጆርናሉ ማናጀር በዶ/ር ተስፋሁን መሰለ የቀረበ ሲሆን ገለጻውን ተከትሎ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፤ የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦችም ከተጋባዥ እንግዶች ተነስተዋል ፡፡