
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራቂ የህክምና ተማሪዎች የመስክና የቡድን የተግባር ልምምድ ፕሮጀክቶች ተመረቁ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ዙር የመስክና ቡድን ስልጠና /TTP /Team Trening Program/ በአራት ቡድን ተመድበው በወጡ የህክምና ተመራቂ ተማሪዎች ግንቦት 5/ 2015 ዓ/ም በወረታ ሳይት የተሰሩ ትንንሽ ፕሮጀክቶች ተመረቁ ፡፡
በምረቃ መርሀግብሩ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአካዳሚክ ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ፣ የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን ነርስ ትምህርት ክፍል ሃላፊ እና የቡድኑ አስተባባሪ ጋሻቸው ባይለየኝ፣ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል የጤና ስርአትና ፖሊሲ መምህር እና የቡድኑ አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ተሻለ፣ የወረታ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህርና ለተግባር ልምምድ የወጡ ተማሪዎች ተገኝተዋል።

እነዚህ ተመራቂ ተማሪዎች በአራት ቡድን ተከፍለው በቲወሪ ያካበቱትን እውቀት ለተግባር ልምምድ ወደ መስክ በመውጣት በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመለየት ለችግሮቹም ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ በመፈለግ 3 ፕሮጀክቶችን ሰርተዋል ብለዋል የቡድኑ አሰተባባሪ አቶ ጋሻቸው ባይለየኝ ። እነዚህም በወረታ ከተማ ለመዋዕለ ህፃናት ት/ቤት ምቹ መፀዳጃ ቤት እና ገበያ ላይ አገልግሎቱ ተቋርጦ እነሰ ፈረሰርሶ የነበረውን የህዝብ መፀዳጃ ቤት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እድሳት በማድረግ ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ እና ጥበቃ ተቀጥሮላቸው ገበያ ለሚውሉ ተጠቃሚዎች ብር 3 በማስከፈል ዘላቂነት ባለው መንገድ ፕሮጀክታቸውን አጠናቀው ማስረከባቸውን የቡድኑ ተጠሪ ተማሪ መሰንበት ገልፀዋል።
እነዚህ የ5ተኛ ዓመት የህክምና ተመራቂ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እየተማሩ በነበሩበት ሰዓት እንደ ሀገር የተለያዩ ችግሮች በተከሰቱበት ወቅት እንደ ኮቪድ 19 ወርሽኝና በሀገራችን በነበረው ጦርነት የሰላም እጦት በመማር ማስተማሩ ላይ ተፅዕኖ የነበረበት ወቅት ስለነበር እነዚህን ተቋቁመው ለዚህ መድረሳቸውን የኮሌጁ የአካዳሚክ ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ አመስግነዋል። አክለውም ይህንን ሁሉ ፈተና አልፈው ይህንን የመሰለ የማህበረሰብ ፕሮጀክት በመስራታቸው ጥንካሬአቸውን አድንቀዋል።

አጠቃላይ የነበራቸው ቆይታና የተሰሩ ስራዎች በዝርዝር በተማሪ መሰንበት ቀርቧል፡፡
በመጨረሻም ተማሪዎች ፕሮጀክቶችን ለመስራት በአይነትና በገንዘብ እንዲሁም በሀሳብ ድጋፍ ያደረጉ ግለሰቦችንና ተቋማትን አመስግነው የእውቅና እና የምስክር ወረቀት ያበርከቱ ሲሆን፤ በተግባር ልምምዱም የላቀ ተሳትፎ ለነበራቸው ተማሪዎች የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ ፕሮግራሙ ተጠናቋል። ፕሮጀክቶቹንም አስመርቀው ለተጠቃሚዎች አስረክበዋል፡፡
