
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር የሚያደርገውን ዝግጁነት የሚገመግም የባለሙያዎች ቡድን ስራውን ጀመረ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር ያለውን ተቋማዊ ዝግጁነት በዝርዝር ለመገምገም ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር የተላኩ ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ዛሬ ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው የመግቢያ ስብሰባ አካሂዷል። በዚህ መድረክ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮችና የሥራ አስፈፃሚዎች ተገኝተዋል።

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነጻነታቸውን በማረጋገጥ የትምህርት ጥራትን እንዲያሰፍኑ፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የጎላ ሚና እንዲጫወቱ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የራስ ገዝነት ሽግግር መርሃ-ግብር ቀርጾ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ2019 ዓ.ም ወደዚህ ሙሉ የራስ ገዝነት አስተዳደር ለመሸጋገር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተለዩትና የቀደምትነት ታሪክ ካላቸው ዘጠኝ ቀዳሚ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ዛሬ የተጀመረው የዝግጁነት ግምገማም ተቋሙ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ መብትና ኃላፊነት ከመረከቡ በፊት ያለውን ተጨባጭ አቅም ለመመዘን የተዘጋጀ ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
ገምጋሚ ልዑኩ በቆይታው ዩኒቨርሲቲውን ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር በአካዳሚያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በፋይናንስና የሰው ሀብት አስተዳደር የተዘጋጁትን ከ46 በላይ ልዩ ልዩ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና ደንቦችን እንደሚመረምርና የተለያዩ የልህቀት ማዕከላትን፣ ላብራቶሪዎችንና ቤተ-ሙከራዎችን እና ሌሎች የመሠረተ-ልማት አደረጃጀቶችን እንደሚጎበኝ ከተደረገው ገለጻ ለማወቅ ተችሏል።ገምገሚ ቡድኑ ከዚህም በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲውን መምህራንና፣ ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች የዩኒቨርሲቲውንና የአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮችን እንደሚያነጋግር በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ ተገልጿል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን ለልዑካን ቡድኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ባደረጉት ንግግር የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ የሕክምናና የከፍተኛ ትምህርት ተቋምነት ልምዱን መሠረት በማድረግ ባለፉት አምስት አመታት ለዚህ ታሪካዊ ሽግግር የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን፣ ስትራቴጂካዊ እቅዶችንና የውስጥ መመሪያዎችን ሲያዘጋጅ መቆየቱን አስረድተዋል። ይህ የራስ ገዝነት ሽግግር ዩኒቨርሲቲው ይበልጥ ውጤታማና ለሀገር ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ተቋም እንዲሆን አዲስ በር የሚከፍት በመሆኑ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አስረድተዋል።
ፕሬዚዳንቱ በመጨረሻም ለገምጋሚ ቡድኑ ተልዕኮ መሳካት የዩኒቨርሲቲው ማህበረስብ በአጠቃላይና ማኔጅመንቱ በተለይ አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

*****************
ለልህቀት እንተጋለን!
የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ሚያዚያ 10/2018 ዓ/ም



