የመስክና የቡድን ስልጠና (TTP) ፕሮግራም በወጡ ተመራቂ ተማሪዎች የተሰሩ ትንንሽ ፕሮጀክቶች ተመረቁ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ2015 በጀት ዓመት የ1ኛው ዙር የመስክና ቡድን ስልጠና (TTP) ፕሮግራም በወጡ ተመራቂ ተማሪዎች ግንቦት 5/ 2015 ዓ/ም በቆላድባ፣ በጠዳ፣ በወረታና በደባርቅ ከተሞች የተሰሩ ትንንሽ ፕሮጀክቶች የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተመረቁ ፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመስክ የቡድን ስልጠና (TTP) ፕሮግራም፣ ተማሪዎቹ የቲቲፒ ቢሮ በሚያዘጋጃቸዉ የዳሰሳ ጥናት መጠይቆች መሰረት በየተመደቡበት አካባቢ የሚኖረውን የማህበረሰብ ችግር ለመፍታት በማረሚያ ቤቶች ፣ በትምህርት ቤቶች ፣በጤና ጣቢያዎች፣ በሀይማኖት ተቋማት እንዲሁም ሰዎች በጋራ በሚኖሩባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በመገኘት ዳሰሳዊ ጥናቱን አካሂደው ችግሮቹን ይለያሉ፡፡ ችግሮቹ ከተለዩ በኋላ ደግሞ እነኝህን የማህበረሰብ የጤና ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ፕሮጀክቶች በመንደፍና ልዩ ልዩ አጋር አካላትን በማፈላለግ ፕሮጀክቶችን በመስራት የማህበረሰቡን ችግር ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲፈቱ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
በያዝነው ዓመት በ2015 ዓ/ም በመጀመሪያው ዙር ደግሞ በተለያዩ የቲ ቲ ፒ ሳይቶች በወጡ የጤና ሳይንስ ተማሪዎች የተሰሩ ትንንሽ ፕሮጀክቶች የተመረቁ ሲሆን፣ በቆላ ድባ ከተማ በጤና ጣቢያው ተበላሽቶ የቆየን መፀዳጃ ቤት በማፅዳትና በማስተካከል፣ የውሃ ማጠራቀሚያ በማስገጠምና የሴትና የወንድ ብሎ በመለየት ወደ ስራ እንዲገባ ማድረግ መቻሉን በተማሪዎች ተወካይ በኩል በሪፖርት ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም በቆላድባ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት የቆሻሻ ማስወገጃ( ማቃጠያ) ሰርተው በማስረከብና ለቆላድባ ወህኒ ቤት የእስረኞች ልብስ በፍል ውሃ ማፅጃ በርሜል በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች አስረክበዋል፡፡
በጠዳ ከተማ ደግሞ ለህዳሴ 2ተኛ ደረጃ ት/ቤት የመጀመሪያ ርዳታ መስጫ እና የሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ ክፍል በተማሪዎች ጉልበት የሙያ ተዋፅኦና በማህበረሰቡ ድጋፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርተው ለተጠቃሚዎች ማስረከብ መቻላቸውን የ5ተኛ ዓመት የህክምና ተማሪና የቡድኑ አስተባባሪ በሆነችው በተማሪ ሊዲያ መኮነን አጠቃላይ የነበራቸው ቆይታና የተሰሩ ስራዎች በዝርዝር ቀርቧል፡፡
ይህ የመስክ የቡድን ስልጠና (TTP) ፕሮግራም ተማሪዎችን ከትምህርታቸው ጋር ቀጥታ የሚያገናኝ፣ በህብረት መስራትን የሚያስለምድና የተለያዩ ባህሪያት ያሏቸው ተማሪዎች በአንድ ሃሳብ ላይ ተሰባስበው ውጤታማ ፕሮጀክት በየአመቱ የሚሰሩበት መሆኑን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናናጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ነፃነት ወርቁ መርሃ ግብሩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል፡፡ በቀጣይ ያላለቁ ትንንሽ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁና ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ እንዲሁም ቀደም ሲል የተሰሩ ፕሮጀክቶች ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የመከታተል ስራ እንደሚሰራ ዶ/ር ነፃነት ያነሱ ሲሆን፣ የቲ ቲ ፒ ሳይቶች ያሉባቸው የከተማ አስተዳደር አካላት በጤና ሳይንስ ተማሪዎች ሊሰሩ ይገባቸዋል የሚሏቸውን ስራዎች ቀደም ብለው ከማህበረሰቡ ጋር በመምከር ሊለዩ እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡
የመስክና ቡድን ስልጠና (TTP) ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት መ/ር ጋረደው ታደገ በበኩላቸው ተማሪዎች እስካሁን ከነበሩት የቲ ቲ ፒ ጊዚያት በአሁኑ ዓመት እጅግ ብዙ ችግሮች የታዩበት እንደሆነ አውስተው፣ ተማሪዎች ይህንን ችግር ተቋቁመው በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬታማ መሆን በመቻላቸው ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል፡፡ ወደፊት ወደ ስራው ዓለም በሚቀላቀሉበት ጊዜም ለሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዴት ቅድሚያ መስጠትና መለየት እንዲሁም መፍታት እንደሚችሉ ትምህርት ያገኙበት እንደሆነ መ/ር ጋረደው አክለው ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ተማሪዎች ለተሰሩ ፕሮጀክቶች በተለያዬ መንገድ ድጋፍ ያደረጉ ግለሰቦችንና ተቋማትን አመስግነው የምስክር ወረቀት ያበርከቱ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹን አስመርቀው ለተጠቃሚዎች አስረክበዋል፡፡