ለቱሪዝም ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ትብብር ለቱሪዝም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የድጋፍ ና ክትትል ባለሙያዎች በደብረ ማርቆስ ከተማ ከግንቦት 17-20/2008 ዓ.ም ስልጠና ተሰጠ፡፡

በስልጠናው የክልሉን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ልዑል ዮኃንስን ጨምሮ ወደ 400 የሚጠጉ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን መድረኩን በንግግር የከፈቱት አቶ ልዑል ዮኃንስ ለዚህ ስልጠና መካሄድ ትብብር ያደረጉ አጋር አካላትን አስመልክተው በተለይ በክልሉ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ለህብረተሰቡ አንገብጋቢ ችግሮች ፈጥኖ በመድረስ የሚታወቀው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአስር በላይ አሰልጣኝ መምህራንን በመላክና ለስልጠናው የሚያስፈልገውን ግማሽ ወጭ በመሸፈን የክልሉን ቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳደግ ላደረገው ቀና ትብብር ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ለአራት ከታታይ ቀናት የተሰጠው ይህ ስልጠና በሶስት ዋና ዋና ርእሶች ዙሪያ ማለትም በቅርስ ጥበቃ ና እንክብካቤ ፣በሙዝየም አጠባበቅ፣ በሆቴል ኦፕሬሽን ናደንበኛ አያያዝ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና የተሰጠ ሲሆን የስልጠናውን አላማ በተመለከተ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ልንገርህ እንደገለጹት ይህ ስልጠና በተለይ ቱሪዝም ካለው ሁለንተናዊ የሃገር ፋይዳ አንጻር ለመስኩ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ማሳደግና ከሌሎች አጋር አካለት ጋር ያለን መልካም ግንኙነት ማሳደግ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስተባባሪነት በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኘውን የምስራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ እየተባለ የሚጠራን ና የቱሪስት መዳረሻ ቦታ ፣ጮቄ ተራራን ፣ አሰልጣኝ መምህራን የጎበኙ ሲሆን ቦታው ካለው የቱሪስት መስህብነት ናአካባቢያዊ ፋይዳ አንጻር ትልቅ ጥበቃ ናትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡
ዘጋቢ፡ ደስታው ዋኘው

