መቅደላ 150 ጉባዔ፣ ከደብረ ታቦር ዳግማዊ ቴዎድሮስ መታሰቢያ ሀውልት ምረቃ በዓል በኋላ
ከደ/ታቦር ዳግማዊ ቴዎድሮስ መታሰቢያ ሀውልት ምረቃ በዓል በኋላ፣ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሰብሳቢ ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ከሆኑት ከዶ/ር ሂሩት ካሳው፣ በክልሉ ከሚገኙ ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች እና በክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚያስተምሩ የታሪክ ምሁራን ጋር በመጪው ሚያዚያ 2-5/2010 ዓ.ም የሚከበረውን ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ መስዋዕት የሆኑበትን ቀን/ የመቅደላን የ150ኛ ዓመት ታሪክ በሚመለከት ጥር 29/ 2010 ዓ.ም በደ/ታቦር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት አዳራሽ በተካሄደው ጉባዔ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የመታሰቢያ በዓሉ ዝግጅት ለአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ የሚተው ሳይሆን፣ የፌደራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የዞንና የወረዳ ሙያተኞችና አመራሮች፣ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፣ በአጠቃላይ የሀገሪቱ ዜጎች በጋራ በመጣመር ለጀግናውና ታሪክ ሁሌም ለማይረሳቸው ለመይሳው ካሳ ያለንን ክብር በምንችለውና በተሰማራንበት የሙያ ዘርፍ አፄውን ሊያስታውስና ሊያወድስ የሚችል የመታሰቢያ በዓል ለማዘጋጀት የበኩላችንን አሻራ ማስቀመጥ፣ ታሪካዊና ሀገራዊ ግዴታችን ነው ያሉት፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የወቅቱ የአማራ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሰብሳቢ ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ናቸው፡፡
[widgetkit id=8274]
አባ ታጠቅ የተወለዱበት ቋራ፣ ያደጉበትና የቄስ ትምህርት የተማሩበት ደንቢያ፣ የንግስና ክብራቸውን ያገኙበት ደረስጌ ማርያም፣ መድፍ በማሰራት የቴክኖሎጅ ስራዎችን የጀመሩበትና ማዕከላዊ መንግስትን የመሰረቱበት ደብረታቦር/ጋፋት እንዲሁም በመጨረሻ የተሰውበት መቅደላን ጨምሮ ሁሉም ለቱሪስት መስህብነት እንዲውሉ ጠንክረን መስራት አለብን በማለት ዶ/ር ደሳለኝ በአንክሮ ተናግረዋል፡፡ ይንንም ለማሳካት ከላይ የተጠቀሱት የመንግስትና የሀገሪቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሀገራዊና ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በድጋሚ አሳስበዋል፡፡ የሀገራችን ታሪኮች በብዛት የውጪ ሀገር ዜግነት ባላቸው ጽሐፍት ተጽፈው እንድናነብ ይደረጋል፤ ነገር ግን ሀገራችን ላይ የተሰሩ ታሪኮች በራሳችን መንገድ በመጻፍ፣ በመዘከር ብሎም በመሰነድ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ አለብን ብለዋል፣ ዶ/ር ደሳለኝ፡፡
ከዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ታሪክ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የታሪክ ቦታዎች ላይ የተለያዩ ታሪካዊ ምልክቶችን በማስቀመጥና ግንባታዎችን በመገንባት ለቱሪስት መስህብነትና ለታሪክ ቅርስነት እንዲውሉ ለማድርግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና የፓርኮች ልማት ቢሮ ሀላፊ ክብርት ዶ/ር ሂሩት ካሳው ናቸው፡፡ ዶ/ር ሂሩት የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮ የ150ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓልን በተመለከተ ከቋራ – መቅደላ ድረስ በዝግጅቱ ወቅት የሚደረግ የጉዞ አውደ ጥናት እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡ 24 የሚሆኑ የመንግስት እና የግል የሚዲያ አካላት እና የተለያዩ የሀገራችን እውቅ የኪነ ጥበብ ሰዎች በዝግጅቱ ላይ በመሳተፍ የጥበብ ስራቸውን ለማቅረብ ፈቃደኛ መሆናቸውን ደ/ር ሂሩት አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ዝግጅቱን የሚያስተባብረው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ት/ት ክፍል ኃላፊ አቶ ማርሸት ግርማይ አጠቃላይ ዝግጅቱን አስመልክቶ በቅርቡ ጥር 10/2010 ዓ.ም በጎንደር ፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ ለበርካታ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች እና ለቢ.ቢ.ሲ./BBC Amharic ጋዜጣዊ መግለጫ መሰጠቱን አውስተው የመቅደላ 150 ታሪካዊ ዝግጅት ትምህርታዊ፣ ባህልና መዝናኛ እንዲሁም ጉዞን ያካተተ ይዘት እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ ትምህርትን በሚመለከት አሉ የት/ት ክፍሉ ኃላፊ፣ የተለያዩ አፄውን የሚመለከቱ ጹሁፎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በሚኖሩ ምህራን ይቀርባሉ፡፡ ባህልና መዝናኛን በሚመለከት ደግሞ አፄ ቴዎድሮስ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የቁንጅና ውድድር ያደረጉ በመሆናቸው እርሳቸውን ለማስተወስ ባህላዊ ይዘትን የተላበሰ የቁንጅና ውድድር ይደረጋል፤ በቴክኖሎጅም ቢሆን በሀገራችን ብሎም በአህጉራችን ፈር ቀዳጅ በመሆናችው ይህንኑ ለማስታወስ የጥያቄና መልስ ውድድር ይካሄዳል፡፡ የታሪካዊቷ ጎንደር ተወዳጅ የእግር ኳስ ክለብ ፋሲል ከነማ በዓሉን አስመልክቶ ከአቻ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ በማድርግ የዝግጅቱ ድምቀት ይሆናል፤ አፄውን አስመልክተው የተሰሩ የኪነ-ጥበብ ስራዎችም ተመርጠው በበዓሉ ላይ እንደሚቀርቡ የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ ማርሸት አክልው ገልጸዋል፡፡ ጉዞውን በተመለከተ ከቋራ- መቅደላ በርካታ የሀገራችንን የህብረተሰብ ክፍል ባሳተፈ መልኩ እንደሚከናወን አቶ ማርሸት በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
ሁሉም የሀገራችን ህዝብ ባህሉና ወጉ በፈቀደለት መሰረት የራሱን ቋንቋ ተጠቅሞ በጽሁፍ፣ በቲያትር፣ በግጥም፣ በዘፈን፣ በሽለላ፣ ለጀግናው መሪያችን መይሳው ያለውን ክብር የሚገልጽበት ምክንያት፣ ዘመን ተሻጋሪ፣ ሁሌም አንጸባራቂ በሆነው እስከሞት የሚያደርስ የሀገር ፍቅር ወዳድነታቸው፣ የጀግንነትና የኩራት ምንጭነታቸው፣ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ወዳድነታቸው፣ የአንድነት መሰረት በመሆናቸው መሆኑን ሁሉም የታሪክ ሙህራን ይስማማሉ፡፡ እኒህ የምዕተ ዓመቱ ጀግና ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ባለፈው ጥር 6/2010 ዓ.ም ከተወለዱ 200 ዓመታቸው፣ የፊታችን ሚያዚያ 5/2010 ዓ.ም ደግሞ ህይወታቸው ካለፈ 150ኛ ዓመታቸው በመሆኑ በዓሉ ከላይ በጠቀስናቸው ዝግጅቶች በድምቀት ይከበራል፡፡ የሀገራችን ዜጎች በሙሉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዚህ ታሪካዊ በዓል ተሳታፊ ትሆኑ ዘንድ በአክብሮት ተጋብዛችኋል!
በተያያዘ ዜና በደ/ታቦር ዩኒቨርሲቲ ሙሉ ወጪ የቆመው የደብረ ታቦር ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ መታሰቢያ ሀውልት ምረቃ በዓል የኢፌዴሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የእለቱ የክብር እንግዳ ክቡር አቶ ያለው አባተ፣ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች የመንግስትና የግል ተቋማት ኃላፊዎችና ተወካዮች በተገኙበት ጥር 29/2010 ዓ.ም ለምረቃ በቅቷል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሰብሳቢ የሆኑት ደ/ር ደሳለኝ መንገሻ የክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች የአካባቢያቸውን ብሎም የክልላቸውን ማህበረሰብ በማገልገል ለአደረጉት አስተዋጽኦ በተከበሩ አፈ ጉባኤ የምስጋና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ሌሎችም የመንግስትና የግል ተቋማት ኃላፊዎችና በወቅቱ ለምረቃ ለበቁት በደ/ታቦር ከተማ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች በተመሳሳይ የእውቅናና የምስጋና ሽልማት ማግኘታቸውን ከቦታው በመገኘት ለማየት ችለናል፡፡
ዘጋቢ፡- አምሳሉ ግዛቸው
አርታኢ፡- ደምሴ ደስታ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

