ማራኪ ሪቪው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ2007 ዓ.ም ዓመታዊ መፅሄት ለህትመት በቃች
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሃገራችን በቀዳሚነት የጤና ሙያተኞችን ለማፍራት የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅና ማሰልጠኛ ማዕከል በሚል ስያሜ በ1947 ዓ.ም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከተመሰረተ 61 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
ዛሬ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፍሬዎች ከሃገር እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ የስኬት ቁንጮ ላይ የደረሱ የሕዝብን ችግር በምርምር የፈቱ እዉቅ ሳይንቲስቶች ለመሆን በቅተዋል፡፡
በምርምሩ ዘርፍም ሀገራዊና አካባቢያዊ ይዘት ያላቸዉ የህብረተሰብ መሰረታዊ ችግሮች ላይ መሰረት ያደረጉ በርካታ ምርምሮችን በማካሄድ ህብረተሰቡ ከምርምር ዉጤቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆን እያደረገ ይገኛል፡፡
ዩኒቨርሲቲዉ ህብረተሰቡን ማገልገል ቀዳሚ ዓላማ አድርጎ እንደመመስረቱ፤ ህዝቡ ዉስጥ ዘልቆ በመግባት ከህብረተሰቡ ችግሮች ቅድሚያ የሚሰጠውን በመለየት በመምህራንና በተማሪዎች የሚሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎት በብዛት በጥራትና በተደራሽነት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በአንድ ግቢ የተጀመረው የማሰልጠን ስራ ዛሬ ላይ የዩኒቨርሲቲውን የኮሚኒቲ ትምህርት ቤትና የ620 መምህራን መኖሪያን ጨምሮ የሰባት ትልልቅ ግቢዎች ባለቤት ሆኗል፡፡
በ60 ዓመታት ጉዞዉ ዩኒቨርሲቲው ያስመዘገባቸዉን ድሎች ዕዉቅና እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ለዚህ ዉጤታማ ጉዞ፤ ለድሎችና ለስኬቶች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ድጋፍ ላደረጉ አጋር አካላት ዕዉቅና ለመስጠት፣ ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበትን ደረጃና እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ለማስተዋወቅና በዚህ ወርቃማ አጋጣሚ በመጠቀም የወደፊቱ ስራ ዉጤታማ ይሆን ዘንድ የነበሩ የሃገር ዉስጥና የዉጭ ግንኙነቶችን ለማጠናከር፤ አዳዲስ ግንኙነቶችን ለመፍጠር፤ ባጠቃላይ የተቋሙን የወደፊት ዕድገት በፅኑ መሰረት ላይ ማቆምን ዋናና መሰረታዊ ዓላማ አድርጎ የ60ኛ ዓመት የአልማዝ ኤዮቤልዩ በዓሉን በድምቀት ከተበረ ማግስት ያሳለፈነው 2007 ዓ.ም የተገኙ ጠቃሚ ግብአቶች ተቀምረው እጅግ ዘርፈ ብዙ የሆኑ አመርቂ ተግባራት የተከናወኑበት ነበር፡፡
ማራኪ ሪቪው ዓመታዊ የዩኒቨርሲቲው መፅሄት ይህንን የዩኒቨርሲቲውን ጉዞ ለማስቃኘት በርካታ ቁምነገሮችን በፅሁፍና በምስል ይዛለች፡፡ ከርቀትም ከቅርብም ያላችሁ ከመፅሄቷ በርካታ መረጃ ታገኛላችሁ ብለን እናምናለን፡፡ ከስኬቶቻችን ጀርባ ምንጊዜም እናንተ አላችሁና ተግባሮቻችንን ለእናንተው ከማድረሻ መንገዳችን አንዱ ይኼው በመሆኑ እንካችሁ ብለናል፡፡ መፅሄቷ በህትመት የምትሰራጭ ቢሆንም ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በዌብ ሳይታችን በሶፍት ኮፒ በአማራኛውና በእንግሊዝኛው በኩል እንዲጫን አድርገናል በዚህም መፅሄቷን በማንበብ ያላችሁን አስተያየት በኢሜል uogpir@gmail.com ወይም demissedesta@yaho.com ላኩልን

