ስለካይዘን ስራ አመራር ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተቋማዊ ለውጥ ማስተባበሪያ ዳይሬክተሬት ከጎንደር ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ለ55 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የስራ ክፍል አመራሮችና ፈፃሚወች በካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍና ዙሪያ በዩኒቨርሲቲ እንግዳ ማረፊያ ከሰኔ 02-03/2008 ዓ.ም የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታከለ ታደሰ ስልጠናው ወቅታዊ እና ወሳኝ መሆኑን ተናግረው ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አስር አመታት ከፍተኛ ለውጥ ቢያመጣም አሁንም የሀብት ብክነት መኖሩን ገልፀው ይህም የሆነው የካይዘንን ስርአት በአግባቡ ባለመፈጸም ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ታከለ ታደሰ የምርምርናማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት
የካይዘን ስርአትን ለመተግበር ደግሞ የእውቀት፣ የክህሎትና የልምድ ችግር ሳይሆን የአፈፃፀም ችግር በመኖሩ ምክኒያት እንደሆነ እና ስልጠናው ይህን ክፍተት እንደሚሞላ ያላቸውን ተስፋ በመግለፅ ስልጠናውን መስጠት ብቻ ሳይሆን ውጤት እንዲመጣ ብሎም የመጣውን ለውጥ ለመገምገም የምያስችል ስርአት በመዘርጋት ክትትል እና ድጋፍ ይደረግ ብለዋል፡፡

አቶ ፈንታሁን ጫኔ የተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተቋማዊ ለውጥ ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈንታሁን ጫኔ ስልጠናውን አስመልክተው ሲናገሩ ካይዘንን በትክክል ለመተግበር ተከታታይ የሆን ስልጠና እና ፈቃደኛ የሰው ሀይል ዋነኛ መሳሪያዎች መሆናቸውን ገልፀው በዩኒቨርሲቲው ማተሚያ ቤትና ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት በተሻለ ሁኔታ እየተፈፀመ መሆኑንና በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከብክነት መዳኑን ገልፀዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አያይዘው ስልጠናወች ካሁን በፊት የተሰጡ ቢሆንም በዩኒቨርሲቲው የሚጠበቀውን ያህል ለውጥ ማምጣት ያልቻሉት ስልጠናወች ለውስን ሰልጣኞች ብቻ በመሰጠቱና የካይዘን ትግበራ በየስራ ክፍሎች ባለቤት ማጣት እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ይሁን እንጅ አሁን የተሰጠው የካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍና ስልጠና ካሁን በፊት ይሰጡ የነበሩ ስልጠናወች ያልመቱትን ግብ ይመታሉ ምክንያቱም ሰልጣኞች ከተለያዩ የስራ ክፍሎች የተወከሉ በመሆናቸውና ከስራ ክፍሎች ስር ለሚገኙ ሌሎች ሰራተኞች ስልጠናውን መስጠት የሚያስችላቸው ግንዛቤ ከማግኘታቸው በተጨማሪ እነዚህ ሰልጣኞች ለስራ አመራር ፍልስፍና ተፈፃሚነት ተጠያቂ መሆናቸው ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ካይዘንን ለመተግበር የሚያግዱ ተግዳሮቶችን በመለየት፣ የተለያዩ ጥያቄወችን በመጠየቅና በመመለስ፣ በከጎንደር ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በተደረገ የመስክ ምልከታ እና በዩኒቨርሲቲው ወርክሾፖች በተከናወኑ የተግባር ሰራዎች ስልጠናው ተጠናቋል፡፡

ሰልጣኞች በመስክ ምልከታ ላይ
ዘጋቢ፡መሰረት አለምነህ
አርታኢ፡ ደምሴ ደስታ

