ስለ እናት ንብ አረባብ ዘዴ ስልጠና ተሰጠ
በስሜን ጎንደር ዞን በዳቫት ወረዳ ለሚገኙ ለ50 አርሶአደሮችና ለ10 የግብርና ባለሞያዎች የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና ፋካሊቲ ከስሜን ጎንደር ዞን የእንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ስለ እናት ንብ አረባብ ዘዴ በዳቫት ወረዳ አስተዳደር አዳራሽ ከግንቦት 5-6/2008 ዓ.ም ስልጠና ተሰጠ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና መምህርና የፋካሊቲዉ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ እረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት አቶ ማለደ ብርሀን ዩኒቨርሲቲዉ እንደሚታወቀዉ ከመማር ማስተማሩ ጎን የህብረተሰብ ግልጋሎት መስጠት አንዱና ዋነኛዉ ተልዕኮ በመሆኑ ፋካሊታቸዉ በርካታ የማህበረሰቡን ክህሎትና አመለካከት ለማሳደግ የሚረዱ ስልጠናዎችን በተለያዩ ዘርፎች በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አዉስተዋል፡፡ በተጨማሪም በንግግራቸዉ ምንም እንኳ በአማራ ክልል ብሎም በስሜን ጎንደር ዞን ከሌሎች ክልሎችና ዞኖች የበለጠ የማር ምርት ቢኖርም ነገር ግን ህብረተሰቡ ከምርቱ የሚገባዉን ያክል ተጠቃሚ አይደለም ብለዋል ስለሆነም ህብርተሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ የስልጠናዉ ዋና አላማ መሆኑን ለሰልጣኞች አሳዉቀዋል፡፡

በመቀጠል የእለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የዳቫት ወረዳ ተወካይ አስተዳዳሪ አቶ ዳንኤል ታርቀኝ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በወረዳዉ ለሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተደጋጋሚ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን በማድነቅና አሁን ደግሞ በንብ ማነብ ላይ ለተሰማሩ አርሶአደሮችና ለግብርና ባለሞያወች ለተዘጋጀዉ ስልጠና ደስተኛ መሆናቻዉን በመግለጽ ሰልጣኞች ስልጠናዉን በትኩረት በመከታተልና ከስልጠናዉ በኋላም የሰለጠኑትን ተግባራዊ በማድረግ ወረዳዉ ከማር ምርት ማግኘት ያለበትን ጥቅም እንዲያገኝ አሳስበዋል፡፡

ስልጠናዉ በጽንሰ-ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ሲሆን ስልጠናዉን የሰጡት የስሜን ጎንደር ዞን የእንሰሳትና ሀብት ልማት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽ/ቤት ባለሞያ አቶ ሀይሉ ብርሃኑና ፕሮፌሰር ማለደ ብርሃን ሲሆኑ ስልጠናዉ ከአንድ ወገን በአሰልጣኞች ብቻ የሚሰጥ አለመሆኑን ገልጸዉ ሰልጣኞች ያሏቸዉን እዉቀትና ልምድ እርስ በርስ እንዲለዋወጡም ጭምር በማሳሰብ ወደ ስልጠናዉ ገብተዋለል፡፡

ሰልጣኞች በስልጠናዉ ወቅት ንግስት ንቦችን እንዴት ማራባት ወይም ማባዛት የሚያስችል እዉቀትን ገብይተዋል፡፡ በተጨማሪም ወደ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ለመሸጋገር የሚረዳ የሽግግር ቀፎ እንዴት እንደሚሰራና ለንቦች መራባት ወይም መባዛት አስቸጋሪ ለሆኑት የቁንጫጭና የጉንዳን መከላከያ ዘዴን በስልጠናዉ ወቅት በግልጽ ለማየት ችለዋል፡፡

ስልጠናዉን አስመልክቶ ከሰልጣኞች መካከል የዳቫት ወረዳ የእንስሳት ሀብት ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተፈሪ አለሙ አንደተናገሩት ስልጠናዉ የማር ምርትን ለማሳደግ የሚረዳ የሽግግር ቀፎ የአሰራር ሂደትን በማየታቸዉና የሽግግር ቀፎዉ በቀላሉ በአካባቢያቸዉ በሚገኙ ነገሮች የሚሰራ በመሆኑ በስልጠናዉ ያገኙትን ዕዉቀት በቀላሉ ለሌሎች እንዲሸጋገር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል::
እንዲሁም የዳቫት ወረዳ የወቅን ዙሪያ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር ችሎት ካሳ ስልጠናዉ ስለ ንብ ማባዣ የሽግግር ቀፎ አሰራር እንዲያዉቁ ስለረዳቸዉ እጅግ መደሰታቸዉን ገልጸዉ ከስልጠናዉ በኋላ የግላቸዉን የሽግግር ቀፎ በመስራት የማር ምርታቸዉን እንደሚያሳድጉ በሙሉ እምነት ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡ አምሳሉ ግዛቸዉ

