ቅርሶቻችንን ማስመለስ ብቻ ሳይሆን ያሉንን ቅርሶች መጠበቅና መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ
በመሳፍንት ተከፋፍላ የእርስ በእርስ ሽኩቻ፣ ፉከክርና ግጭት በዝቶባት ለህዝቦቿ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ላይ የነበረችን ሀገር አንድ ያደረጉ ዘመን ተሻጋሪ ንጉስ ፣ የሚሊኒየሙ ጀግና፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያ አባት፣ በአለም ስማቸው ካሳ ሀይሉ፣ በጦር ስማቸው መይሳው ካሳ፣ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣ በንግስና ስማቸው ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ የሚሉ በርካታ ስያሜዎች የተሰጣቸው የኪነጥበብ ሰዎች፣ በሙዚቃ፣ በግጥም፣ በተውኔት ስማቸውን የሚያነሱት ታላቁ ንጉስ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት ዝክረ ሰማዕት መታሰቢያ ከሚያዚያ 2-8/2010 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
በዓሉ ሚያዚያ 2 እና 3/2010 ዓ.ም ለሁለት ቀናት ያህል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዝግጅቶች ከተከበረ በኋላ ቀጣዩን መርሃ ግብር የደብታቦር ዩኒቨርሲቲ አከብሯል፡፡ ከጎንደር የተነሳው የበዓሉ አከባበሩ ተሳታፊ ቡድን ደብረታቦር ከተማ ሲደርስ በበርካታ ፈረሰኞች የታጀበ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ ፈረሰኞቹም በአጅባር ሜዳ የፈረስ ጉግስ ትርዒት በማሳየት ታዳሚውን አዝናንተዋል፡፡
[widgetkit id=8888]
በዕለቱ የኢፌድሪ ባሀልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወ/ማርያም፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳው፣ የደብረታር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታደሰ ይርዳው፣ የደብረታር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው፣ የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሰብሳቢ እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች፣ ም/ፕሬዚዳንቶች እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በዕለቱ በሀገር ውስጥ እና ከባህር ማዶ በመጡ ምሁራን “በአንድነት ላይ የተመሰረት ጠንካራ፣ ዘመናዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ላይ የአጼ ቴዎድሮስ ጅማሮች” በሚሉና ሌሎች ከንጉሱ ጋር የተገናኙ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ሰፊ ዉይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
በተጨማሪም የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክቸር ትምህርት ክፍል ባልደረቦች እና በሺገዝ አማካሪዎች አማካኝነት ኤግዚቪሽን፣ ሙዚየም፣ ጋለሪ፣ ስቶር፣ ላይብረሪ፣ የአስሩም በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ማዕከላትን ጨምሮ ሌሎችንም በርካታ ክፍሎችን የያዘ የአፄ ቴዎድሮስ ፋውንዴሽን የመጀመሪያ ምዕራፍ የህንፃ ዲዛይን ቀርቦ አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ነግሰው በቆዩባቸው ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ አንድነት ከማስጠበቅ ጀምሮ ሀገራችንን ወደ ማማ የሚያወጡ አያሌ ተግባራትን የሰሩ ባለ ራዕይ መሪ ናቸው፡፡ ጎልተው ከሚነሱ አንፀባራቂ ስራዎቻቸው መካከልም ለቴክኖሎጂ መስፋፋትና ማደግ የነበራቸው ጉጉትና የጀመሯቸው ዘመን ተሻጋሪ ስራዎቻቸው ይገኙበታል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የሚገጥሟቸውን የውጭ ወራሪ ኃይል ለመከላከል የሚያስችል በዘመናዊ መንገድ የተደራጀ የጦር መሳሪያ አቅም የሌላቸው መሆኑን ተገንዝበው ይህንን ችግር ለመፍታት በዘመን ተሻጋሪው ራዕያቸው በመመራት የመጀመሪያው የአፍሪካ የኢንደስትሪ ውጤት የሆነውን ከ6000 – 8000 ኪ.ግ ክብደት ያለው በአውሮፓ ሚሲዮናውያን እስረኞች የተሰራው የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ትልቁ ሴባስቶፖል መድፍ የተሰራበት ቦታ ጋፋት ላይ ጉብኝት ተደርጓል፡፡ በዚህም ንጉሱ መድፉን ሲያሰሩበት የነበረው በአካባው የሚገኙ የተለያዩ ጥሬ ዕቃዎች፣ የብረት ዝቃጭ፣ እንዲሁም የጊዚያዊ ቤተ-መንግስት ፍርስራሽ ተጎብኝቷል፡፡
ይህ ስፍራ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ከመመስረቱ ከስምንት ዓመታት በፊት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቦታውን ማጥናት የጀመረ ሲሆን፣ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመ በኋላም ለዩኒቨርሲቲው ማስረከቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ስም ሲነሳ አብሮ የሚነሳውና በዘመናቸው ላስመዘገቧቸው ስኬቶችም ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የጦር ጀኔራላቸው ፊታውራሪ ገብርየ ነው፡፡ የገብርየ የትውልድ ቦታ ራስ ጋይንት ሲሆን፣ የአካባቢው ህዝብ እጅግ በደማቅ አቀባበል እና በልዩ መስተንግዶ እንግዶችን ተቀብለው አስተናግደዋል፡፡
በመቀጠልም ከተንታ ወረዳ ከተማ አጅባር 29 ኪሎ ሜትር እና ከደሴ 157 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ የምትገኘው ”መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ” በተባለበት የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የመጨረሻዎቹ የስንብት ሰዓታት ላይ ትልቅ ገድል የተፈፀመበት፤ ስለ ሀገር አንድነት ስለ ዘመናዊ ኢትዮጵያ፣ ታላቁን ንጉስ ጨምሮ በርካቶች በጀግንነት የወደቁባት የመቅደላ አምባ መዳረሻ ላይ በመገኘት ጉብኝት ተደርጓል፡፡ ንጉሱ በጀግንነት እራሳቸውን የሰውበት ስፍራ፣ የመቃብር ቦታ፣ ዕቃ ግምጃ ቤት፣ ቤተ መንግስት፣ የውጊያ ምሽግ እንዲሁም በእንግሊዝ ጦር ተዘርፎ የሄደው በኋላም በብዙ ጥረት ወደ ሀራችን ተመልሶ በአደራ አዲስ አበባ የሚገኘው ታቦተ መድሃኒያለም ቤተክርስትያን ፍርስራሽ እና እጅግ በርካታ ቁጥር ባለው የሰው ኃይል ከጋፋት ወደ መቅደላ ንጉሱ ያስወሰዱት የሴባስቶፖል መድፍ እና ሌሎችንም የበዓሉ ተሳታፊዎች ጎብኝተዋል፡፡
በመቀጠልም የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እና ሌሎችም በርካታ እንግዶች በተገኙበት የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
የዚህ በዓል ተባባሪ አዘጋጅ የሆነው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አዲስ አበባ ላይ በአዘጋጀው ሲምፖዝየምም፣ የኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ዶ/ር ሂሩት ወ/ማርያም፣ በተወካዮች ምክር ቤት የባህልና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳው፣ የአማራ ክልል የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሰብሳቢ እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የታሪክ ምሁራን፣ አርቲስቶች እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በዚህ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት በተካሄደበት ሲምፖዝየም በዕለቱም ቅርሶቻችንን በማስመለስ ሂደት ላይ መወሰድ ስላለበት ስልት እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ትኩረት ሰጥተን በመስራት የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ፀጉር፣ የልዑል አለማየሁ አፅም፣ የእቴጌ ጥሩወርቅ ልብስን ጨምሮ በኢንግሊዝ ሀገር ሙዚየሞች የሚገኙ በርካታ ንዋየ ቅድሳት፣ የብራና መፃህፍቶች፣ የወርቅ መስቀሎች እና ሌሎችንም ንብረቶች እንዲመለሱ ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንዳለበት ተገልጿል፡፡ እንዲሁም ቅርሶቻችንን ማስመለስ ብቻ ሳይሆን፣ በሀገራችን የሚገኙ ቅርሶቻችንን መጠበቅ እና መንከባከብ ብሎም የቅርስ ጥበቃ እና ደህንነት የወንጀለኛ መቅጫ የህግ ማዕቀፎችንም መፈተሸ እንደሚገባ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ የቱሪዝም አገልግሎቶች እና የመሰረተ ልማት አውታሮችን ማጠናከር፣ የእደ ጥበብ ማዕከላትንም በማቋቋም ታሪክ እና ባህላችንን ማጉላት እንደሚያስፈልግም ተነስቷል፡፡
በዕለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ከቋራ እስከ መቅደላ ድረስ የነበረውን የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ በአቀረቡት ጽሁፍ እጅግ ሰፊ ንቅናቄ መፈጠር መቻሉን ጠቅሰው፣ ከንቅናቄው በኋላም በማህበረሰቡ እና ከወረዳ እስከ ፌደራል ድረስ በመንግስት አካላት ትልቅ መነሳሳት መፈጠር መቻሉን አንስተዋል፡፡
ሀሳቡን ከማመንጨት ጀምሮ በባለቤትነት በአማራ ክልል የሚገኙ አስሩን የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የክልሉን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና የፌደራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎችንም አካላት በማሳተፍ ትልቅ መነቃቃት እንዲፈጠር የአንበሳውን ድርሻ ወስዷል ማለት ይቻላል፡፡ እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በፅንሰ ሃሳብ ብቻ ማስተማር ሳይሆን፣ በተግባር የታሪክ መዘክሮችን በማሳየት ባህልን በማጉላት እና ማንነትን በማስተዋወቅ ረገድ ታሪክ መስራት የቻለው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ምስጋና ተችሮታል፡፡
በመጨረሻም ከታሪክ ተመራማሪዎች፣ ከኪነጥበብ ሰዎች፣ ከንጉሱ ቤተሰብ አባላት፣ ከኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ፣ ከአርበኞች ማህበር እና ከዩኒቨርሲቲዎች በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ የሚመራ ዘጠኝ አባላት ያሉት ጊዚያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ ይህ የኮሚቴ አባል ቅርስ የሚያስመልስ ቋሚ ኮሚቴ አፈላልጎ ለማዋቀር የተደራጀ ነው፡፡ በዚህም የዳግማዊ አፄቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት ዝክረ ሰማዕት መታሰቢያ በዓል የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቋል፡፡
በቀጣይ የተፈጠረውን ንቅናቄ በማስቀጠል የታላቁ ንጉስ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘመን ተሻጋሪ ራዕይ ዕውን እንዲሆን፣ የተፈጠረው መነቃቃትም በጋለ ስሜት እንዲቀጥል፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርሻ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ተገልጿል፡፡
ዘገባ – ደጄ አማረ

