በሀር ትል አረባብ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በባዮሎጅ ትምህርት ክፍል ከደንቢያና ጭልጋ ወረዳዎች ለተውጣጡ ስራ ፈላጊ ወጣቶች የሀር ትል በማርባት የሀር ክር ምርትን ለማግኘትና ለማሳደግ የሚያሰችል ስልጠና በማራኪ ግቢ በሚገኘው የቤተ-ሙከራ ክፍል ሰኔ 14/2008 ዓ.ም ሰልጠና ተሰጠ፡፡

የስልጠናው ፕሮጀክቱ አዘጋጅና አቅራቢ አቶ ወንድሜነህ ጀንበሩ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልገሎት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከደንቢያ እና ጭልጋ ወረዳ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ጋር በመነጋገር ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸውን እና ቁርጠኛ የሆኑ ስራ ፈላዎች እንዲመለመሉ ከተደረገ በኃላ በሀር ትል አረባብ ዙሪያ የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ሰልጣኞች በሚገኙባቸው ወረዳዎች መሰጠቱንና በስልጠናውም ከሰልጣኞች፣ከወረዳዎች እና ከዩኒቨርሲቲው የሚጠበቁ ጉዳዮችን በዝርዝር ውይይት መደረጉን እና በውይይቱም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሀር ትል እንቁላሎችን፣መራቢያና መመገቢያ ቤቶችንእንደሚያቀርብና ወረዳዎች የቤተ ሙከራና የቦታ ጥያቄዎችን እንደሚያቀርቡእንዲሁም የገንዘብ ጥያቄዎች ከጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ጋር በመነጋገር የሚፈታ መሆኑን በመነጋገር መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የሀር ትል እንቁላሉን ከአዋሽመልካ በማምጣት ተገባራዊ ሥልጠናውን በማረኪ ግቢ መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡

አቶ ወንድሜነህ ጀንበሩ አያይዘው እንደገለፁልን የስልጠናው አላማ የሀር ትልን በመጠቀም ራሳችንን ችለን ልብስ መስራት የሚያስችልና ለማህበረሰቡን የስራ እድል የመፍጠር ስልጠና መሆኑን አስረድተዉ የገበያ ሁኔታው ከፍና ዝቅ የማለት ችግር ቢኖርም ሰልጣኞች በቁርጠኝነት ከሰሩና አስፈላጊ የሆነ ክትትልና ሙያዊ ድጋፍ ከተደረገላቸው ስራው አዋጭብሎም ወደ ኢንዱስትሪ ሊቀየር የሚችል ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ በስልጠናው ተገኝተው ለሰልጣኞች ባስተላለፉት መልእክት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲመሰረት የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ሲሆን አሁንም አገልግሎቱን በመቀጠል የእውቀት ሽግግር በማድረግ ሰልጣኞች በሚገኙባቸው ወረዳዎች በመገኘት ተከታታይ የሆነ ስልጠና እንደሚሰጥ እና ከስልጠናው በተጨማሪ የመመገቢያ እና የማራቢያ ሞዲሎችን ሰርቶ በማቅረብ፣ ሰልጣኞች ብዙ ወጭ እንዳያወጡ ሊረዱ የሚችሉ ጣውላወችን ብረታብረቶችን እንደሚያቀርቡ ገልፀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ለወረዳ አመራሮች በቂ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠትና የገበያ ትስስር በመፍጠር በኩል ወጣቶቹ ለውጤት እስከሚደርሱና ራሳቸውን ችለው እስከሚሰሩ ከጎናቸው እንደሚሆኑ ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ስራው ጊዜን እና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ዉጤቱ ወዲያዉኑ ላይማጣ ስለሚችል ሰልጣኞች በትግስት እና በቁርጠኝነት ጠንክረረው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
አንዳንድ ሰልጣኞች በበኩላቸውም ስልጠናው በበቂ ሁኔታ ቢሰጥም አዲስ እና እንግዳ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተከታታይ የሆነ የሙያ ድጋፍ የማይደረግ ከሆነ ምንአልባት ስልጠናው ከስልጠና ፍጆታነት ባልዘለለ ውጤት ላያመጣ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ መሰረት አለምነህ
አርታኢ፡ ኤሊያስ መንበሩ

