በሀገራችን ያለውን የስርዓተ ምግብ ክፍትት ለመሙላት እየተሰራ ነው
በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለይም በአማራ ክልል ከፍተኛ የሆነ የስነ ምግብ ክፍትት መኖሩን የስነ-ምግብ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ይህን የስነ-ምግብ ክፍተት በተወሰነ መልኩ ለመሙላት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከኮሶዬ ልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር በሰሜን ጎንደር በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች፣ ህብረተሰቡ ያለውን ትንሽ ቦታ ተጠቅሞ የጓሮ አትክልትን እንዲያተክል፣ እንዲመገብ ብሎም ሽጦ የገቢ ምንጭ እንዲያገኝ፣ የማስተማር፣ የማሰልጠን እንዲሁም የጓሮ አትክልት ዘርን የማሰራጨት እና በአቅራቢያው እንዲያገኝ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ታዲያ ይህንን መልካም ተሞክሮ ወደ ሌሎች ወረዳዎች እና ዞኖች በማስፋት በክልል ደረጃ ፕሮግራሙን ለማስቀጠል በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የየድርሻቸውን ወስደው ማህበረሰቡ ዘንድ ተደራሽ ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ዓለም አቀፍ አውደ ጥናት የካቲት 16 እና 17/2010 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ HDP አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
አውደጥናቱ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳሬክቶሬት ጽ/ቤትና በኮሶየ ልማት ፕሮግራም የጋራ ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ኮሌጅ ምክትል ዲን ዶ/ር አስማማው አለሙ፣ የኮሰየ ልማት ፕሮግራም ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አንድሪው ካርልሰን፣ በአማራ ክልል ከሚገኙ አስሩም ዩኒቨርሲቲዎች ጥሪ የተደረገላቸው መምህራን እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
[widgetkit id=8457]
አውደጥናቱን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከኮሶዬ የልማት ፕሮግራም ጋር በጋራ እየሰራው ያለው ስራ እድገት አበረታች በመሆኑ ይህንን መልካም ተሞክሮ በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋት ዩኒቨርሲተው ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰር መርሻ አክለውም ማህበረሰባችን የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገብ ግንዛቤ መፍጠር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሀላፊነት መሆኑንና ዩኒቨርሲቲዎችም ማህበረሰቡን በማገልገልና በማስተማር የበኩሉን መወጣት እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ በአውደ ጥናቱ ቁልፍ ንግግር/keynote speech/ ያደረጉት ዶ/ር አስማማው በበኩላቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ኮሌጅ ለሚያደርጋቸው በርካታ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጅ ሽግግር ስራዎች ከሀገር ውስጥ ከሚገኙ እና ከተለያዩ አለምአቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር ግንኙነቶችን በመፍጠር ለስትራቴጅዎች ስኬት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለዚህም ከኮሶዬ ልማት ፕሮግራም ጋር ዩኒቨርሲቲው ያለው የረጅም አመት ትብብር ለማህበረሰቡ የአመጋገብ ስርዓት መሻሻል ለሚሰራው ስራ እንደ አብነት የሚጠቀስ ግንኙነት ነው ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል የሚገኙት አስሩም ዩኒቨርሲቲዎች ይህንን መልካም ተሞክሮ ወስደው እንደ ዩኒቨርሲቲ የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን የአመጋገብ ስርዓት ክፍተት ለመሙላት የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝበው ችግሩን ለመቅረፍና የየራሳቸውን ድርሻ እንዲወስዱ በቡድን ውይይትና እና በመስክ ላይ ጉብኝት ተነሳሽነት የመፍጠር ስራ ተሰርቷል፡፡
በአውደ ጥናቱ ዙሪያ አስተያየት የሰጡን አቶ ረታው ሞትባይኖር የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ እና የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አብይ መንክር፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየሰራ ያለውን መልካም ተሞክሮ ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለማጋራት ያዘጋጀውን ወርክሾፕ ዩኒቨርሲቲው ምን ያህል ህብረተሰቡን እያገለገለ እንደሚገኝ የሚያሳይ እና ዩኒቨርሲቲው ለተቋቋመበት አላማ የቆመ መሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ፕሮግራሙን ለማሳካት ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥና ፕሮግራሙን ወደፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት እንደሚሰራና የህብረተሰቡን የጓሮ አትክልት የመመገብ ባህል ለማሻሻል ተጨማሪ ስራዎች እንደሚሰሩ ተገልፆ አውደጥናቱ ተጠናቋል፡፡
ዘጋቢ፡ መሰረት አለምነህ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

