በህዋ ሳይንስ የጥናትና ምርምር ተግባር ከፍተኛ ትም/ት ተቋማት ድርሻቸው የጎላ መሆኑ ተገለፀ
በሰሜን ወሎ ዞን በላሊበላ ላስታ ወረዳ የሚገኘውን የአቡነ ዮሴፍ የጠፈር ምርምር ጠቢያ እና በግዳን ወረዳ የሚገኘውን የአቡኃይ ጋራ (ለምድ ጣቢያ) የጠፈር ምርምር ጣቢያ ባለበት ሁኔታ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ወደ ጎንደር ዩኒቨርቲ፣ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ ወልድያ ዩኒቨርሲቲና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለማዘዋወር የካቲት 09/2008 ዓ.ም የጋራ መግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስነ-ስርዓት በላሊበላ ከተማ ላይ ተከናወነ፡፡
በዕለቱ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የበላይ ጠባቂ አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ክንዳያ ገ/እግዚያብሔር፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ እና የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቅ በጋራ የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙ ሲሆን በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የተጀመረው ዓለም አቀፍ የጠፈር ምርምር ጣቢያ የመገንባት ቅድመ ጥናት የሆነውን ትልቅ ፕሮጀክት ውጤታማ አድርጎ ለማስቀጠል የጥናትና ምርምር ስራ በዘላቂነት መስራት የሚችሉት ዩኒቨርሲቲዎች በመሆናቸው የተጀመረውን የተጠናከረ የምርምር ስራ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ለዩኒቨርሲቲዎች አስረክቧል፡፡
የጥናትና ምርምር ስራው ዋና ዓላማ ከባህር ወለል በላይ 4200 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው የአቡኃይ ጋራ (ለምድ ጣቢያ) እና ከባህር ወለል በላይ 4300 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው በአቡነ ዮሴፍ ሰንሰለታማ ተራራ ላይ የሚገኘውን ቦታ ዓለም አቀፍ የጠፈር ምርምር ጣቢያ መሆን መቻል አለመቻሉን ማረጋገጥ ሲሆን ለጠፈር ምርምር መሆን ባይችል እንኳ አካባቢው በተፈጥሮ የታደለውን ዕምቅ ሀብት በመጠቀም ሌሎች በርካታ ሳይንሳዊ ምርምሮች ሊካሄዱ የሚችሉበት ቦታ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እንደሆነና በዚህ የጠፈር ምርምር ተግባር ላይ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻቸው የጎላ በመሆኑ ይህንኑ ባለቤትነት ይዘው የምርምር ስራውን አጠናክረው በማስቀጠል ሁለቱ ማዕከላት ዓለም አቀፍ የጠፈር ምርምር ጣቢያ መሆን መቻልና አለመቻላቸውን በጥናት በማስደገፍ ለሚመለከተው አካል እንዲያሳውቁ ለማድረግ ለማስቻል እንደሆነ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የበላይ ጠባቂ አቶ ተፈራ ዋልዋ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡

የጋራ መግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስነ-ስርዓት ከፊል ገፅታ
በሁለቱ ሳይቶች የሚካሄደው የምርምር ስራ በአራቱም ዩኒቨርሲቲዎች ተመራማሪዎች የሚደረግ ጥናት ሲሆን በተመራማሪዎች ገለፃ ቦታዎቹ ዓለም አቀፍ የጠፈር ምርምር ጣቢያ መሆን የሚያስችላቸውን የመጀመሪያ ደረጃ ማለትም ከመሬት በጣም ከፍ ብሎ መገኘቱ እና ከግርዶሽ ነፃ መሆኑ፣ ግልፅና የጠራ ሰማይ መኖሩ፣ የቦታው አቀማመጥ ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ አለመሆኑ እና ከአካባቢ ብካይ የፀዳ ከመሆኑ በተጨማሪ ሌሎችም መስፈርቶች አሟልቶ የተገኘ በመሆኑ ወደፊት ለሀገራችን እጅግ በጣም ተስፋ ሰጪ መሆኑና ጣቢያዎቹ በትክክልም ዓለም አቀፍ የጠፈር ምርምር ጣቢያ መሆን ከቻሉ ሀገራዊ ጥቅሙ የጎላ መሆኑ በጣቢያዎቹ ላይ በመስራት ላይ የሚገኙት ተመራማሪዎች ገልፀዋል፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብም ይህ ፕሮጀክት በቦታው ላይ ስራ በመጀመሩ የመንገድ፣ የውኃ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን የቻለ ሲሆን ከጥናትና ምርምር ስራው የሚፈለገው ውጤት ማግኘት ከተቻለ ሃገራችን ለሌሎች የዓለም ሃገራት ዳታ መሸጥ፣ ቴሌስኮፕ ለመትከልና ቦታውን ለሳይንሱ ለመጠቀም ቦታ ማከራየትና በርካታ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ እጅግ በጣም ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑ ፕሮጀክቱ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄን የሚመልስ ሌሎቹ ሀገራት ከደረሱበት የእድገት ጎዳና ደርሰን እንድንራመድ የሚያስችል ለውጤታማነቱም ከፍተኛ ትግልና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ፕሮጀክት መሆኑን ተመራማሪዎች ገልፀዋል፡፡

ተመራማሪዎች ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች ሙያዊ ማብራሪያ ሲሰጡ
የአቡኃይ ጋራ እና የአቡነ ዮሴፍ የጠፈር ምርምር ጣቢያዎችን የጎበኙት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ እንደተናሩትም “ቡድኑ ሁለቱንም የአቡኃይ ጋራ እና የአቡነ ዮሴፍ የጠፈር ምርምር ማዕከላት መጎብኘቱ ተመራማሪዎች ምን አይነት ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመው እየሰሩ እንደሆነ እንድንረዳ ከማስቻሉም ባለፈ ከዚህ በኋላም በሚኖረው የምርምር ስራ ተመራማሪዎች ችግር እንዳይገጥማቸው በምንችለው ሁሉ ድጋፍ የምናደርገበትን ሁኔታ ለመፍጠር ምቹ አጋጣሚ ነው፡፡ ካሉ በኋላ፤ አራቱም ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ የሚያደርጉት ምርምር በቀጣዮቹ ሁለትና ሶስት ዓመታት እድለኛ ሆነን ቦታው ዓለም አቀፍ የጠፈር ምርምር ጣቢያ መሆን ከቻለ ከሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ሃገራዊ ፋይዳ ባለፈ በዓለም ውስጥ በጠፈር ምርምር ከተሳተፉ ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ ሊያሰልፈን የሚችል ታላቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ ቦታው ለህዋ ምርምር መሆን ባይችል እንኳ በርካታ ተመራማሪዎች ስለ ቦታው ምንም አይነት ግንዛቤ የሌላቸው በመሆኑ መጥተው የቦታውን እምቅ ሃብት እንዲያዩትና የምርምር ሃሳቦችን እንዲያፈልቁ ለማድረግ በቀጣይ የሚሰራ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በዋድላ ወረዳ በማሄ ተራራ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ መሪነትና ሙሉ ባለቤነት የጠፈር ምርምር ማዕከል የቅድመ ጥናት ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የአቡነ ዮሴፍ ተራራ ጫፍ ከባህር ወለል በላይ 4300 ጫማ ከፍታ
ጎንደር ዩኒቨረሲቲ በሳይንስና ምርምር ዘርፍ በርካታ ተግባትን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን በሰሜን ወሎ ዞን በላሊበላ ላስታ ወረዳ በአቡነ ዮሴፍ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ እና በግዳን ወረዳ በአቡኃይ ጋራ (ለምድ ጣቢያ) ላይ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የጠፈር ምርምር ቅድመ ጥናት ሁለት ወንድና አንድ ሴት የፊዚክስ ትምህርት ክፍል መምህራንን በመመደብ የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፆ በማበርከት ላይ የሚገኝ ሲሆን በተለይም ከአራቱም ዩኒቨርሲቲዎች በብቸኝነት ሴት ተመራማሪን የመደበው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲሆን እጅግ በጣም አስቸጋሪ እና ከፍተኛ ብርድን ተቋቁሞ ለመስራት ፈታኝ በሆነ አካባቢ፤ ቤተሰቦቿንና ልጆቿን ትታ ለዚህ ሀገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ ለሆነ የምርምር ስራ ቅድሚያ በመስጠት ስራዋን በትጋት እየተወጣች የምትገኘው መምህርት ሰላማዊት ሻወል፤ ሴት ልጅ ምንም ሳይበግራት በሁሉም መስክ በመሳተፍ ውጤታማ መሆን እንደምትችል ለሴት ተማሪዎቻችን እና መምህራን አርአያ መሆን የቻለች ጠንካራ ሴት መሆኗን በቦታው በተገኘን ጊዜ ለማየት ችለናል፡፡

መምህርት ሠላማዊት ሻወል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህርትና የህዋ ሳይንስ ተመራማሪ እና ተመራማሪዎች ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች ሙያዊ ማብራሪያ ሲሰጡ
በተለይም በአቡነ ዮሴፍ ተገኝተን ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ በጎበኘንበት ወቅት ከአራቱ ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ ተመራማሪዎች በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ እና በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የበላይ ጠባቂ አቶ ተፈራ ዋልዋ አማካኝነት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቲ-ሸርቶች፣ ኮፍያ እና የመሳሰሉት በስጦታ የተበረከቱላቸው ሲሆን ተመራማሪዎችም በስጦታው ደስተኛ መሆናቸውንና ለቀጣይ ስራቸው መነቃቃትን እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል፡፡

የህዋ ሳይንስ የቅድመ-ጥናትና ምርምር ቡድን አባላት የጥናትና ምርምር ቡድን አባላት በጉብኝቱ ከተሳተፉ እንግዶች ጋር

