በሆቴል ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያጋጥሙ የአመለካከት ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ስር የሚገኘው የሆቴል አስተዳደር ትምህርት ክፍል የመጀመሪያውን አመታዊ ሴሚናር ህዳር 12/2010 በማራኪ ግቢ ድህረ ምረቃ ህንፃ ቲያትር አዳራሽ አካሄደ፡፡ በሴሚናሩ በጎንደር ከተማ በሆቴል ስራ ላይ ያሉ ኃላፊዎች፣ ከአዲስ አበባ፣ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ኃላፊ፣ ከጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም ተጋበዥ እንግዶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የኮሌጁ ዲን አቶ ሀይማኖት በላይ፣ የኮሌጁ ምክትል ዲን ዶ/ር ደምስ አላምረው፣ የኮሌጁ ተማሪዎችና መምህራን ተገኝተዋል፡፡
[widgetkit id=7579]
የሆቴል ኢንዱስትሪው በአደጉ ሀገሮች እንደ ዋንኛ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚታይ ሴክተር ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ግን ለኢንዱስትሪው የሚገባውን ትኩረት ሲሰጥና ዘርፉም በሰለጠኑ ባለሙያዎች ሲታገዝ አይታይም፡፡ በመሆኑም የሆቴል አስተዳደር ትምህርት ክፍል በሆቴል ዘርፍ ያሉ ተማሪዎች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት፣ በአጠቃላይ በማህበረሰቡ ያሉ ከአመለካከትና ከዕውቀት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ይህ ዝግጅት መካሄዱን የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ ሰያር ያሲን ገልፀዋል፡፡ ሴሚናሩ በየአመቱ የሚቀጥልና የባለሀብቶችን፣ የባለሙያዎችን፣ በአጠቃላይ የባለ ድርሻ አካላትን ግንዛቤ በማሳደግ፣ በሆቴሉ ዘርፍ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ትምህርት ክፍሉ የበኩሉን እንደሚወጣ አቶ ሰያር አያይዘው ተናግረዋል፡፡
በሴሚናሩ በሆቴል ኢንዱስትሪው ላይ ያለውን ክፍተት በተለይ በግንባታ ሂደትና አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማሟላት ላይ የሚታዩ ችግሮችን፣ ሆቴሎች የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲሁም የሆቴል ኢንዱስትሪው በዘርፍ ለሰለጠኑ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሌላው ማህበረሰብም ያለውን ጠቀሜታ የሚያሳዩ 4 ያህል ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበዋል፡፡ በቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፎች በሆቴል ኢንዱስትሪው ያሉ ችግሮች ተነቅሰው ወጥተው ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ ይሆናሉ በተባሉ ሀሳቦች ላይም ውይይት ተደርጓል፡፡
ሰሚናሩን ሲካፈሉ ያገኘናቸው የጎሀ ሆቴል ስራ አስኪሂያጅና የጎንደር ከተማ ሆቴሎች ማህበር ሊቀመንበር፣ አቶ አማረ አጥናፉ ትምህርት ክፍሉ ይህንን ሰሚናር አዘጋጅቶ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን እንዲጤኑ ማድረጉ የሚበረታታ ነው ካሉ በኃላ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርቱን በንድፈ ሀሳብ ከመስጠት ባሻገር የመማሪያ ሆቴል በመክፈት በተግባር ልምምድ ተማሪዎችን ቢያግዙ መልካም ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ገልፀዋል፡፡
በሆቴል ኢንዱስትሪው በሀገሪቱ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ሀይል ችግር ለመፍታት ሆቴሎችና በዘርፉ ያሉ ትምህርት ክፍሎች ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸውና ተማሪዎቹን ለተግባር ልምምድ የሚቀበሉ ሆቴሎችም አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ስልጠናው በትክክል እንዲሰጥ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ በውይይቱ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ሆቴሎች ተማሪዎችን ለተግባር ልምምድ ለመቀበል ፈቃደኛ እንዲሆኑ የሆቴል ባለሀብት ማህበሮች ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ ሊሰሩባቸው በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገርና ልምድ በመለዋወጥ ብሎም ስምምነቶችን መፈራረም ተገቢ መሆናቸው በውይይቱ ተነስቷል፡፡
በሴሚናሩ መጨረሻም ለትምህርት ክፍሉ መጠናከርና ለመማር ማስተማር ሂደቱ ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱና በጎንደር ከተማ ለሚገኙ 7 ሆቴሎች የምስጋና የምስክር ወረቀት ከዩኒቨርሲቲው ተበርክቶላቸዋል፡፡ ሆቴሎቹ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉም በሰሚናሩ ማጠቃለያ ላይ የኮሌጁ ምክትል ዲን ዶ/ር ደምስ አላምረው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡ መሰረት አለምነህ
ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

