በመስክ የቡድን ስልጠና /ቲቲፒ/ ለተግባራዊ ልምምድ የወጡ የህክምናና ጤና ሳይንስ ተማሪዎች በማህበረሰቡ ውስጥ የሰሯቸውን አነስተኛ ፕሮጀክቶች አስመረቁ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ2010 ዓ.ም ተመራቂ እና 5ኛ ዓመት የህክምና ተማሪዎች ለስድስት ሳምንታት ያህል ለተግባራዊ ትምህርትና ልምምድ ወጥተው መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ዙር የተሳተፉት ተማሪዎች ሚድ ዋይፈሪ፣ ሄልዝ ኢንፎርማቲክስ፣ ኦፕቶሜትሪ/የአይን ሀኪሞች/ እና የአምስተኛ ዓመት የህክምና ተማሪዎች ናቸው፡፡
የትምህርት አንዱ ተቀዳሚ አላማ ችግሮችን በሳይንሳዊ ዘዴ መፍታት መቻል ነው፡፡ ስለሆነም ተማሪዎች በህበረተሰቡ ውስጥ ገብተው መሰረታዊ የሚባሉ የጤና ችግሮችን እንዴት መለየትና መፍተሄ መስጠት እንደሚችሉ በተለያዩ ወረዳዎች በተግባር የአሳዩባቸውን ማህበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክቶች ለአካባቢው ህ/ሰብ በማስረከብ አስመርቀዋል፡፡በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የዩኒቨርሲቲው የመስክ የቡድን ስልጠና አስተባባሪ አቶ ተስፋየ ሀምቢሳ እና የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች ዲን አቶ ሀይሌ ወልዴን ጨምሮ በየአካባቢው የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
[widgetkit id=8918]
ተማሪዎቹ ከሰሯቸው ቅድመ-ጤና መከላከልን መሰረት ያደረጉ የፕሮጀክት ስራዎች መካከል መፀዳጃ ቤቶች፣የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶች፤ ሻወር ቤቶች ፣የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች የሚጠቀሱ ሲሆን የተሰሩትም በቆላድባ፣ ደባርቅ፣ዳባት፣አዲስዘመንና ወረታ ከተሞች ነው፡፡
የፕሮጀክቶቹ መሰራት በርካታ ማህበራዊና ትምህርታዊ ፋይዳ እንደሚኖረው አንዳንድ ተሳታፊ ተማሪዎች፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና የዩኒቨርሲቲው የመስክ የቡድን ስልጠና አስተባባሪ አቶ ተስፋየ ሀምቢሳ ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ የማህበረሰቡን የጤና ሁኔታ ከማሻሻል በተጨማሪ ተማሪዎች በንድፈ-ሀሳብ ያገኙትን ትምህርት ማህበረሰቡን በማስተባበር በተግባር እንዲተረጉሙ ያስችላል፤ እንዲሁም ለወደፊቱ በስራ አለም ወጥተው የሚቀላቀሉበት ህብረተሰብ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለመገንዘብ ያስችላል የሚለውን ሃሳብ ተሳታፊ ተማሪዎቹ ይጋራሉ፡፡
አንዳንድ ተማሪዎች እንደሚሉትም ፕሮጀክቶቹ በየአመቱ የሚሰሩት በተመሳሳይ ቦታ በመሆኑ ስፖንሰር(የገንዘብ ድጋፍ) ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም ቀጣይ ለመስክ የብድን ስልጠና የሚወጡ ተማሪዎች ፕሮጀክቶቻቸውን በሌሎች ያልተደረሰባቸው አካባቢዎች ቢሰሩ ስራቸው የተሻለ ውጤታማ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የመስክ የቡድን ስልጠና አስተባባሪ አቶ ተስፋየ ሀምቢሳ በፕሮጀክቶቹ ርክክብ ላይ በመገኘት የተማሪዎችን ስራ አድንቀው በየአመቱ በተማሪዎች የሚሰሩ ማህበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክቶች በዘላቂነት እንዲቀጥሉ ማድረግ የአካባቢው ማህበረሰብ ኃላፊነት መሆኑን አሳስበዋል፡፡
በደስታው ዋኘው
የህ/ አ/አ/ግ/ ዳይሬክቶሬት

