በቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ታላቅ የኪነ ጥበብ ምሽት ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት “ፍኖተ ጥበብ” በሚል ርዕስ ጥር 20/2008 ዓ.ም በሳይንስ አምባ አዳራሽ ታላቅ የኪነ-ጥበብ ምሽት ተካሄደ፡፡
በዕለቱ ሁለገብ አርቲስት ጌትነት እንየዉ ተጋባዥ እንግዳ ሆኖ የተገኘ ሲሆን፤ የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ አንተነህ ወርቅነህ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸዉ “የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰው በተለያዩ ጊዚያት የተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦችን በመጋበዝ ቲያትሮችን ለመድረክ ማብቃቱን እንደዚሁም በተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ ዩኒቨርሲቲያችን በማስተዋወቅ ረገድ የራሱን አስተዋፆ ማበርከቱን ገልፀዋል፡፡

አቶ አንተነህ ወርቅነህ የት/ት ክፍሉ ኃላፊ አርቲስት ጌትነት እንየው
የዕለቱን ዝግጅት በንግግር የከፈቱት የሶሻል ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ አይሸሽም ተረፈ በበኩላቸዉ “ትምህርት ክፍሉ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ የኪነጥበብ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንና በተለይም ጎንደር ከተማ የታሪክና የጥበብ ማህደር እንደመሆኗ ብዙ ያልተነኩ የማህበረሰቡን ወግ፣ ባህል፣ የአኗነዋር ዘይቤና ማንነት አጉልተው የሚያወጡ ስራዎች እንዲሰሩ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፤ ካሉ በኋላ ትምህርት ክፍሉ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ከፍተኛ አመራሩና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ላደረገው አስተዋፅዖ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ አርቲስት ጌትነት እንየው ዩኒቨርሲቲው ያቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ወደ ዩኒቨርሰቲያችን በመምጣቱ ያላቸውን ምስጋናም አያይዘው አቅርበዋል፡፡

አቶ አይሸሽም ተረፈ የሶሻል ሳይንስ ና ስዕነሰብ ኮሌጅ ም/ዲን
በዝግጅቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና ሰራተኞች፣ ዲኖችና የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች እንዲሁም ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን አርቲስት ጌትነት እንየዉ “ልባችን ይናገር” የሚል መሳጭና ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጽ ግጥሙን ለታዳሚው አቅርቧል፡፡ በመቀጠልም ለተማሪዎችና በአጠቃላይ የዝግጅቱ ታዳሚዎች ለነበሩ የዩኒቨርሲው ማህበረሰብ አባላት ልምድና ተሞክሮን ይቀስሙበት ዘንድ የአርቲስቱ የህይወት ታሪክ አጠር ባለ መልኩ በመምህር መላኩ አለምነዉ አማካኝነት ቀርቧል፡፡

በዕለቱ ተማሪዎች ቲያትሩን ሲያቀርቡ
በሁለገቡ አርቲስት ጌትነት እንየው የተፃፈው “ጣይቱ” የመድረክ ቲያትር በቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች አማካኝነት ለዕይታ ቀርቦ ከታዳሚዎች አድናቆትን ተችሯል፡፡
የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የከተማዋን የኪነጥበብ እድገት ለማፋጠን በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን በያዝነው የ2008 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅ ታውቋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፈተና ማዕከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የአካዳሚክ ም/ፕሬዝዳንት ተወካይ የሆኑት አቶ ወንድወሰን ካሳሁን ፕሮግራሙን በንግግር ቋጭተዋል፡፡

መምህር መላኩ ዓለምነው አቶ ወንድወሰን ካሳሁን የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ተወካይ የዝጊያ ንግግር ሲያቀርቡ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬ

